ጋዜጠኛ ርዕዮት ዐለሙ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሻካሮቭ ሽልማት የ2013 ዕጩ ሆነው ተመረጡ።

መስከረም ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጋዜጠኛ ርዕዮት ዐለሙን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን  እና አሜሪካዊው  ኤድዋርድ  ስኖውደንን ጨምሮ  ሰባት  ሰዎች የአውሮፓ ህብረት ለነፃነት ታጋዮች በየአመቱ ለሚያዘጋጀው የ “ሻካሮቭ ሽልማት” የ2013  ዕጩ ሆነው ተመረጡ።

የአውሮፓህብረት የሻካሮቭ ሽልማት ኮሜቴ-ከህብረቱ የውጪ ጉዳይና ልማት ኮሚቴ እና ከሰብዓዊ መብት ንዑስ ኮሚቴ ጋር በመሆን ትናንት ሰኞ ይፋ እንዳደረጉት  ማላላ ዩሳፍዛይ ከፓኪስታን፣ ኤድዋርድ ስኖውደን ከ አሜሪካ፣ርዕዮት ዓለሙና እስክንድር ነጋ ከ ኢትዮጵያ፣ አሌስ ቢያላትስ ኪ፣ኤድዋርድ ሌበር፣ እና ሚኮላስታትኬቪች ከቤላሩስ፣ ሚካኤል ኮድ-ኦርኮቭስኪ ከሩሲያ  ሲታጩ በቡድን በቅርቡ ቱርክ የነፃነት መናፈሻ እንዳይፈርስ ድምፃቸውን ያሰሙ ተቃዋሚዎች እና የሲ.ኤን.ኤን የነፃነት ፕሮጀክት ታጭተዋል።

የመጨረሻዎቹ ሦስት ዕጩዎች ከ15 ቀን በኋላ የፊታችን መስከረም 20  ቀን የሚለዩ  ሲሆን፤አሸናፊውም  መስከረም 30 ቀን በሚደረገው የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ ስብሰባ ይፋ እንደሚሆን  ከህብረቱ መግለጫ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አሸናፊው፤ ህዳር 11 ቀን በምስራቅ ፈረንሳይ በምትገኘው ስትራስበርግ ከተማ  በሚዘጋጀው ሥነ-ስርዓት ላይ ሽልማቱን ይቀበላል።

በ አውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባል በሚስ አና ማርያ ጎሜዝ የተጠቆሙት ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ ጥቆማቸው በሌሎች 40 የፓርላማ አባላት ድጋፍ ማግኘቱ፤ ሽልማቱ  ከሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሊያልፍ እንደማይችል አመላካች ነው ሲሉ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በሻካሮቭ ሽልማት አሸናፊ የሚሆኑ ከሚቀዳጁት ክብር በተጨማሪ  እስከ 50 ሺህ ዩሮ የሚደርስ የገንዘብ ሽልማትም ይበረከትላቸዋል።

የ ኢትዮጵያ ሳተላይት ራዲዮና ቴሌቪዥን ለርዕዮት ዓለሙና ለስክንድር ነጋ መልካም ዕድል ይገጥማቸው ዘንድ ልባዊ ምኞታቸውን ይገልጻሉ።