መስከረም ፪(ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የዩኒስኮና የ’ኢንተርናሽናል ዊመንስ ሚዲያ ፋውንዴሽን’ ሽልማቶች አሸናፊ የሆነቸው ታዋቂዋ ፀሀፊና መምህር ርእዮት አለሙ በእስር ቤት የጀመረቸውን የረሀብ አድማ የቀጠለች ሲሆን፣ በእስር ቤት የሚገኙ ሌሎች እስረኞች እያሰቃዩዋት መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል።
በግፍ የታሰረቸው ርእዮት ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑዋ የሚደርስባት ስቃይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ስልት ርእዮት ከእናትና አባቷ እንዲሁም ከነፍስ አባቷ በስተቀር ሌሎች ሰዎች እንዳይጠይቋት የተላለፈውን መመሪያ በመቃወም የረሀብ አድማውን መጀመሩዋ ታውቋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው እናቷ ወ/ሮ አሰለፈች ተክለማርያም ርእዮት የጨጓራ በሽተኛ ብትሆንም በአድማው በመግፋት ምግብ አልቀበልም በማለቱዋ እያለቀስኩ ምግቡን ይዤ ተመለስኩ ብለዋል።
በቅርቡ በሙስና ተከሰው ወደ እስር ቤት የተላኩት ኮሎኔል ሀይማኖት በርእዮት ላይ የስድብ ናዳ ሲያወርዱባት በማደራቸው ርእዮት እንቅልፍ አጥታ ማደሩዋንና ብትሞትም በበሽታ ሳይሆን በእነሱ ምክንያት መሞቱዋን እንዲያውቁት እንደነገረቻቸው ወ/ሮ አሰለፈች ተናግረዋል
ኮሎኔል ሀይማኖት ከርእዮት ጋር እንደማይተዋወቁ ወ/ሮ አሰለፈች ገልጸው፣ ኮሎኔሏ አቤኔዘር ከምትባለዋ የእስር ቤቱ የሴቶች ሀላፊ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸውም ገልጸዋል
በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ ተወካዮች ርእዮትን ለመጠየቅ ቃሊቲ ቢገኙም እንዳያገኙዋት መከልከላቸው ይታወቃል። የማረሚያ ቤት ሀላፊዎችን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።