ነሃሴ ፳፰(ሃያ ስምንት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦባማ አስተዳደር በዜጎቹ ላይ የኬሚካል መሳሪያዎችን በመጠቀም ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ባለው የባሽር አላሳድ መንግስት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ሲያስጠነቅቅ ከቆ በሁዋላ በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ፣ ጉዳዩን ለኮንግረስና ለሴኔት አቅርበው ለማስወሰን በመፈለጋቸው ባለፈው ሳምንት የታየው የጦርነት ደመና ዝናቡን ሳያርከፈክፍ መጥፋቱ ይታወቃል።
ይሁን እንጅ ፕሬዚዳንት ኦባማ የዲሞክራት እና የሪፐብሊካን መሪዎችን ከአነጋገሩ በሁዋላ ፣ ሁለቱም መሪዎች የሰጡዋቸው መልሶች አዎንታዊ መሆን፣ አሜሪካ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ሶሪያን ልትደበድብ ትችላለች የሚለው ግምት አይሏል።
አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ የጀመሩት የሚሳኤል ተኩስ ልውውጥ ውጥረቱን እንደገና የጨመረው ሲሆን፣ በዚህ መሀል ኢራን በጦርነቱ ውስጥ እጃን በቀጥታ ካስገባችን አካባቢው በጦርነት ሊታመስ እንደሚችል ብዙዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
እንግሊዝን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ አገሮች ሶሪያን ለመደብደብ የቀረበውን አማራጭ አይደግፉም። የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ከአሜሪካ ጎን መቆማቸውን ቢያስታውቁም፣ የአገሪቱ ምክር ቤት ድምጽ እንከሚሰጥበት ድረስ በይፋ ጦርነቱን መቀላቀላቸውን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ የሚታየው ውጥረት እየተባባሰ መሄድ የነዳጅ ዋጋን እንዳይጨምረውም ተሰግቷል። በዚሁ ሳቢያ ቀስ በቀስ እያገገመ የሚገኘው የአለም ኢኮኖሚ ተመልሶ ወደ ችግር ሊገባ ይችላል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት የሆኑት ሩሲያና ቻይና የአሜሪካንን እርምጃ በጽኑ ተቃውመዋል።