የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሰራተኞች የፓርቲ ስራ እንደሰሩ መታዘዛቸውን ተቃወሙ

ነሃሴ ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰንደቅ እንደዘገበው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አንዳንድ ሰራተኞች የኢህአዴግ የ2006 እቅድ መስሪያ ቤቱ ካለበት መደበኛ ስራ ውጪ የገዢውን ፓርቲ ድርጅታዊ ስራ በልዩ ሁኔታ እንዲያስፈፅም ማስገደዱን እየተቃወሙ ነው።አብዛኛዎቹ ሰራተኞች ሚኒስቴሩ በ2006 ዓ.ም ድርጅታዊ ስራን ትኩረት ሰጥቶ እንዲተገብር መድረጉ ሰራተኛው ያለፍላጎቱ የመንግስትንና የድርጅትን ስራ ቀይጦ እንዲሰራ የሚያስገድድ ነው ብለዋል።

ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ቅሬታ ያቀረቡት እነዚሁ ሰራተኞች እቅዱን ያለፍላጎታቸው እንዲተገብሩ፤ ካልሆነም የደመወዝ እድገትም ሆነ የደረጃ እድገት የሚያገኙበት ዕድል ዝግ የሚያደርግ መሆኑ ተነግሯቸዋል። ሚኒስቴሩ በሐምሌ ወር 2005 ዓ.ም “የዝግጅት ምዕራፍ ዝክረ ተግባር” በሚል ባለ ስምንት ገፅ እቅድ ላይ በሚኒስቴሩ የድርጅት ስራ ማጠናከር ተገቢ መሆኑን አመልክቷል። በዚሁ እቅድ ውስጥ “ከዚህ ቀደም በነበሩን የሴክተራችን እንቅስቃሴዎች የድርጅት እንቅስቃሴ ጎልቶ የሚታይ ያልነበረ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ በጀት ዘመን ይህ አካሄድ መቀጠል አይኖርበትም። ሴክተራችን የሚመራው መሪ ድርጅታችን ባስቀመጣቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም የነዚህ ተግባራት ተፈፃሚነት ዕውን የሚሆነው ልዩ ልዩ ዘርፎቻችን በውስጣቸው ያለውን የድርጅት እንቅስቃሴ ማጠናከር ሲችሉና አባላትም የሴክተሩን ፖሊሲና ስትራቴጂ ለማስፈፀም ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ሲችሉ ነው። በዚህ በጀት ዘመን በሴክተራችን ይህን ማረጋገጥ ካልተቻለ መሪው ድርጅት በተቋማችን ውስጥ ያለው የመሪነት ሚና እና ውጤታማነቱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ ሆኗል። በመሆኑም በዝግጅት ምዕራፍ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ተግባራት ማከናወን እንደ ወሳኝ አቅጣጫ ሊወሰድና ወደ ተግባር ሊለወጥ ይገባል” የሚል ማሳሰቢያ መጨመሩ ታውቋል። የወረዳ አደረጃጀቱን እንደገና ፈትሾ ማጠናከር፣ በተዋረድ የመሰረታዊ ድርጅትና የህዋስ አደረጃጀቶችን ፈትሾ ማጠናከር፣ በሴክተራችን የድርጅት ዘርፍ የሚታዩ የአቅም ክፍተቶችን በጥንቃቄ በጥናት መለየት፣ ክፍተትን ማዕከል ያደረገ የአቅም ግንባታ ስልጠና ዝግጅት ማከናወን፣ በየደረጃው ለሚገኙ አመራርና የመሪ ድርጅት አባላት የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት፣ የድርጅት ዘርፍ የጠራ ዕቅድ ማዘጋጀት፣ ዕቅዱን ማዕከል በማድረግ ለእያንዳንዱ አመራርና አባላት በተዘረዘረ እቅድ የተደገፈ ግልፅ ተልዕኮ መስጠት፣ የአባልነት መለኪያው በዋነኝነት በዘርፉ እቅድ ሁሉም ምዕራፎች ላይ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኖ መገኘት መሆኑን ማስረፅ፣ ተግባራዊ ማድረግና የክትትልና ድጋፍ አግባብ ዘርግቶ ሂደቱን መከታተልና መደገፍና የመሳሰሉ ተግባራት ለባህልና ቱሪዝም ሰራተኞች የቀረበው ሰነድ ያስረዳል ሲል ሰንደቅ ዘግቧል። ኢህአዴግ በበህርዳር ባደረገው 9ኛ ጉባኤ ላይ የኢህአዴግ አባላት የትግል ቁርጠኝነት እየላላ መምጣቱን በማውሳት የግንባሩን አላማዎች ወደ ተለያዩ የመንግስት መስሪያቤቶች ለማውረድ እና ጠንካራ የ5 ለአንድ አደረጃጀት ለመገንባት መወሰኑ ይታወቃል። የመንግስት ሰራተኞች የኢህአዴግ አባላት ካልሆኑ የትምህርት እድል፣ የደሞዝ ጭማሪ ወይም ሌሎች እድገቶችን እንደማያገኙ አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅቶች ሳይቀር ሲገልጹ ቆይተዋል።