በአዲስ አበባ በሳምንት እንድ ቀን ውሀ ማግኘት ብርቅ የሆነባቸው ሰፈሮች መኖራቸው ተዘገበ

ነሃሴ ፲፫(አስራ ሦስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-  “በሳምንት አንድ ቀን ውሃ ማግኘት ብርቅ የሆነባቸው ሰፈሮች፣ በውሃ እጦት አካባቢያቸውን በመጥፎ ጠረን የሚበክሉ የኮንዶሚኒየም መኖሪያዎች፣ ለተደጋጋሚ አቤቱታ ምላሽ ሳያገኙ በርካታ ወራት እየተቆጠሩ የሚማረሩ ነዋሪዎች የአዲስ አበባ የዘመኑ ገጽታ ሆነዋል” ሲል አዲስ አድማስ ዘገበ

የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ” በቂ ውሃ ስለሌለ በራሽን ለማከፋፈል እየሞከረ” መሆኑን ገልጿል። ባለስልጣኑ ”  የኤሌክትሪክ መቆራረጥና የአንዳንድ ሰራተኞች እንዝህላልነት፣ ለመንገድ ግንባታ የሚቆፈሩ ቧንቧዎች እንዲሁም በከንቱ የሚባክን ውሃ መብዛቱ የውሃ እጥረትን እንዳባባሱ ይናገራል።

የአገሪቱ እንዲሁም የአህጉሪቱ መዲና በሆነችው ከተማ፣  በርካታ ነዋሪዎች የዝናብ ውሃን ደቅኖ ለማጠራቀም ሲሯሯጡና በጀሪካን ተሸክመው ውሃ ሲያመላልሱና የፎቅ ደረጃዎችን ለመውጣት ሲውተረተሩ ማየት የተለመደ ሆኗል የሚለው የአድማስ ዘገባ ፣ በገርጂ፣ አየር ጤና፣ ጀሞ፣ እንቁላል ፋብሪካ፣ አዲሱ ገበያ፣ እንዲሁም በየአቅጣጫው የተገነቡ ኮንዶሚኒየሞችን ጨምሮ በርካታ የከተማዋ ሰፈሮች፣ በውሃ እጥረት የተቸገሩ ነዋሪዎች “አወይ ስልጣኔ” በማለት መላ እንደጠፋባቸው ሲገልጹ ይሰማል ብሎአል።

” ውሃ የሚጠፋበትን ቀን ዘርዝሮ ከመናገር ይልቅ ውሃ የሚመጣበትን ቀን መናገር ፣ በሳምንት አንዴ ውሃ ከመጣ ፌሽታ ነው፤ ብርቅ ይሆንብናል ሲል የአዲሱ ገበያ ነዋሪ የሆነው ልዩነህ አያሌው መናገሩ ተዘግቧል።

አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ወ/ሮ እፀገነት ተስፋ  በአዲስ አበባ የውሃ ችግር መኖሩን አምነው  ዋናው ምክንያትም የውሃ እጥረት ነው  ብለዋል።