ነሃሴ ፲(አስር)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መንግስት ትናንት ሼህ ኑሩን ማን ገደላቸው በሚል ርእስ በኢቲቪ በለቀቀው ዘጋቢ ፊልም ላይ አንድነት ፓርቲ የሼህ ኑሩን ግድያ ደግፎ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲጠራ ማድረጉን የግንቦት7 ልሳን የሆነው ኢሳት ቴሌቪዥንም አሸባሪዎችን ” አይዞአችሁ በርቱ” እያለ ድጋፍ እንደሰጣቸው አንድ ግለሰብን በማናገር አቅርቧል
በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ሶስት ተጠርጣሪ ገዳዮች ቀርበው የሚናገሩ ሲሆን፣ ፊልሙ ከአንዱ ክፍል ተቆርጦ ከሌላው ክፍል እየተገጣጠመ የተቀናበረና ገዳይ የተባሉትም ከፉኛ የተደበደቡ በሚመስል መልኩ ለመናገር ሲቸገሩ ይታያል።
አንድነት ፓርቲ “የሙስሊሞችን ጥያቄና የሼክ ኑሩን ግድያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ማያያዝ ወንጀል ነው” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ዘጋቢ ፊልሙ መቅረቡን በጽኑ ተቃውሞአል።
ፓርቲው ፊልሙ ” የገዥውን ፓርቲ ብፅእና ከመተረክም በላይ ጉልበተኝነትንና ፍረጃን ማእከል አድርጎ ከአኬልዳማ እና ከጃሀዳዊ ሀረካት የቀጠለ በፓርቲያችን እና በዜጎች ላይ የተቃጣ ህገ ወጥ የፕሮፓጋንዳ ስራ ነው” ብሎታል፡፡
የመንግስትነት ስልጣን የያዘ አካል ሀገራዊ ችግሮችን ለምን በዶክመንተሪ ፊልም ለመፍታትና ለማዳፈን እንደሚጥር እንቆቅልሽ ሆኖብናል የሚለው አንድነት ” የሙስሊም ጥያቄ በውይይትና በመግባባት ላይ ተመስርቶ ሊመለስ እንደሚገባና የሀይል እርምጃው መቆም እንዳለበት አሳስቧል።
ፊልሙ የኢህአዴግ የፍረጃ ፖለቲካ የተንፀባረቀበት፤ የተለየ ሀሳብና ጥያቄ ያቀረቡ ግለሰቦችንና ተቋማትን ማሸማቀቅ ብሎም የማጥፋት እኩይ ተግባር ማሳያ መሆኑንም ፓርቲው ገልጿል። አንድነት ፍርድ ቤት በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ አድርጎ ውሳኔ ሳያሳልፍ በቴሌቪዥን ፍርድ መስጠቱ ገዢው ፓርቲ በህግ የማይገዛ አምባገነን ስለመሆኑ ግልጽ ማሳያ ሲሆን የፍትህ ስርዓቱ ልዕልናም በአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ መገፈፉን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት የፓርቲያችን አመራሮች በየግዜው የሚያደርጉትን ንግግሮች ሞያንና ንጹህ ህሊናን በሚያጎድፍ መልኩ እየቆራረጠ ሙሉ ትርጉሙን እንዳይዝ አድርጎ በማስተላለፍ እየፈጸመ ያለው አሳፋሪ ተግባር እንዲታረም፣ በሼህ ኑሩ ላይ የተፈጸመው ግድያ በየትኛውም አካል የተፈጸመ ቢሆንም ህገ ወጥ እና ኢሰባአዊ መሆኑን ፓርቲው ጠቅሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት በክርስቲያኑና በሙስሊሙ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር እየሰራ ነው በማለት አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ለኢሳት ገልጸዋል።
መንግስት በተለያዩ ቀበሌዎች ስብሰባዎችን እየጠራ ክርስቲያኑ ወገን በሙስሊሙ ጥያቄ ፍርሀት እንዲሰማው እያደረገ መሆኑን እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል።
መንግስት በአሁኑ ሰአት በመላ አገሪቱ የሀይማኖት ጉበኤ መክፈቱ ታውቋል።