ነሃሴ ፱(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ ከነሃሴ 1/2005 እስከ መስከረም 25/2005 ዓ.ም ድረስ በዳኞች እረፍት ቀን ምክንያት ዝግ የሚሆን ሲሆን በነዚህ የእረፍት ጊዜያት በአዲስ አበባ ካሉት አስር ምድብ ችሎቶች አምስት ያህሉ በተረኝነት የሚሰሩ ሲሆን በድሬዳዋ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተጠቀሰው ጊዜም መደበኛ ስራውን የሚቀጥል መሆኑን አስታውቆአል፡፡
በዚህም የልደታ እና የኮልፌ ቀራንዮ ምድብ ፍትሀ ብሔር እና የስራ ክርክር ጉዳዮች በልደታ ምድብ ይታያሉ፡፡ የአራዳ ፤ መናገሻ እና አዲስ ከተማ የስራ ክርክር እና ፍትሀ ብሔር ጉዳዮች ደግሞ በአራዳ ምድብ ችሎት ይታያሉ፡፡ የንፋስ ስልክ ላፍቶ እና የቂርቆስ ምድብ የፍትሐብሄር እና የስራ ክርክር ጉዳዮች ደግሞ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ምድብ ችሎቶች ይታያሉ፡፡ የየካ ምድብ ፍትሀ ብሔር እና የስራ ክርክር ጉዳዮች ደግሞ እዛው የካ ምድብ ችሎት ይስተናገዳሉ፡፡ የአቃቂ ምድብ ፍትሀ ብሔር እና ሥራ ክርክር ጉዳዮች ደግሞ በአቃቂ ምድብ ችሎት ለማስተናገድ ማቀዱን ገልጾአል፡፡
የቤተሰብ ችሎት ጉዳይ ያላቸው ባለ ጉዳዮች በልዩ ሁኔታ መደበኛው ችሎት ዘወትር ረቡዕ መስተናገድ የሚችሉ ሲሆን ቤተሰብ ችሎት ቀድሞ በነበረባቸው ምድብ ችሎቶች ማለትም ልደታ፣ ቦሌ፣ አራዳ፣ ቃሊቲ፣ ኮልፌ ቀራንዮ እና ንፋስ ስልክ በመቅረብ መስተናገድ ይችላሉ፡፡ በዚህ ችሎት ክስ መክፈትም ሆነ ሌሎች በመደበኛ ችሎት ይሰሩ የነበሩ ጉዳዮች ይስተናገዳሉ፡፡
በተረኛ የፍትሐ ብሔር ችሎቶች የሚስተናገዱ ጉዳዮች አጣዳፊ የሆኑ እና በወቅቱ እርምጃ ካልተወሰደ የማይተካ ጉዳት ባለጉዳዩ ላይ ያደርሳሉ ተብለው የሚገመቱ ናቸው፡፡
የወንጀልጉዳዮችን በተመለከተ ደግሞ ፈጣን የወንጀል ጉዳዮች ችሎቶች በመደበኛ ችሎት ማለትም ቀድሞ እንደነበረው ከሰኞ እስከ አርብ ባለው ጊዜ በአስሩም ምድብ ችሎቶች ወይንም በሁሉም ምድብ ችሎቶች ባለ ጉዳዮች ቀርበው መስተናገድ ይችላሉ፡፡ በዚሁ ችሎት መደበኛ ወይንም መደበኛ ያልሆኑ የወንጀል ጉዳዮች በእነዚህ ችሎቶች ይታያሉ፡፡
የጊዜቀጠሮ ጉዳዮች ሳምንቱን በሙሉ ማለትም ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በአራዳ ምድብ ችሎት ይስተናገዳሉ፡፡ ዳኞች በእረፍት ጊዜያቸው ለሚቀጥለው አመት የተላለፉ መዝገቦችን የማቃለል ስራም በመስራት ላይ እንደሚገኙ መግለጫው ጠቅሶአል፡፡