33 የፖለቲካ ድርጅቶች በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የተወሰደውን እርምጃ አወገዙ

 

ነሃሴ ፰(ስምንት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የ33 ፓርቲዎች ትብብር ለኢሳት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው መንግስት እየተከተለ ያለው የሀይል እርምጃ በዜጎች ህገመንግስታዊ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ላይ የተፈጸመ ህገወጥ አምባገነናዊ ድርጊት በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ድርጊቱን ሊቃወምና ሊያወግዝ ይገባዋል።

በአገር ቤትና በውጪ ያሉ የመገናኛ ብዙኃን፣ የነጻው ፕሬስ አባላት እና ማኅበራዊ ድረ-ገጾች በህዝበ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ መካከል ያለመተማመን ለመፍጠር ከሚሰራጨው አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ሰለባነት የመታደግና የዘመናት አብሮነቱን የማጠናከር የሙያና የዜግነት ግዴታና አገራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አሳስቦአል

 

ፓርቲዎቹ ” ገዢው ፓርቲ የተያያዘው አፍራሽ አምባገነናዊ አካሄድ በአገራችንና በዜጎቿ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ተገንዝቦ ከድርጊቱ እንዲታቀብ፣ የሙስሊም ወገኖቻችንን ጥያቄ በኃይል ለመፍታት የሚያደርገውን ህገወጥ እርምጃ  በአስቸኳይ እንዲያቆም፣ የእምነት ነፃነታቸውን በሠላማዊ መንገድ ስለጠየቁ የታሰሩ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣የህገወጥ ድርጊቱ ፈጻሚዎችና አስፈጻሚዎች ለህግ እንዲቀርቡ ” ጠይቀዋል።

 

የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ተቆሪቋሪዎችና የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ አባላት   መንግሥት ለሠላማዊ ትግሉ የአሸባሪነት ታፔላ በመለጠፍ  የሚወስደውን ህገወጥ እርምጃና መሰረተቢስ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ እንዲያወግዙም ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።

 

ፓርቲዎቹ መንግሥት በኃይልና በሴራ ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ ጥያቄዎችን ለማፈን የሚከተለው አካሄድ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊያመራና አገራችንና ህዝቧን የበለጠ የከፋና ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊከት እንደሚችል  አስጠንቅቀው፣ ይህን አስጊ ሁኔታን ለመከላከል የሚቻለው ዜጎች በኃይማኖት ሳይከፋፈሉ የመንግሥትን የኃይል  እርምጃ በጋራ ሲቃወሙና ሲያወግዙ መሆኑን በመግለጫ አትቷል።

ፓርቲዎቹ ያወጡት መግለጫ ጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ የጸጥታ ሀይሎች በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ የወሰዱትን እርምጃ ተገቢና የሚቀጥል ነው መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።

አቶ ሀይለማርያም በስም ባልጠቀሱዋቸው ከሙስሊሙ ጥያቄ ጋር ግንኙነት አሉዋቸው ባሉዋቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ መንግስት እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል።

በተመሳሳይ ዜናም አንድነት ፓርቲ የጀመረውን ህዝባዊ ንቅናቄ ለማስተጓጎል ከፍተኛ አበል በመክፈል ለአባላቱ ስልጠና ማዘጋጀቱን ፍኖተ ነፃነት ዘግቧል።

ኢህአዴግ “አንድነት ፓርቲንና ንቅናቄውን እንዴት ማስቆም ይቻላል” በሚል በከፍተኛ አመራሮቹ ውይይት ካደረገ በኋላ በመላ ሀገሪቱ ፀረ አንድነት ፓርቲ ስልጠና “ጠንካራ” ላላቸው አባላቱ ለመስጠት መዘጋጀቱን ምንጮቹ  ጠቅሶ ፍኖተ ነጻነት ዘግቧል።

ለስልጠናው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መመደቡን የገለጸው ጋዜጣው፣  ኢቲቪና የክልል ሬዲዮ ጣቢያዎችና የመንግስት ጋዜጦች አንድነት ፓርቲ የሸሪአ ህግን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ ከሚንቀሳቀሱ ሽብርተኞች ጋር እየሰራ ነው የሚል የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እንዲከፍቱ ጥብቅ መመሪያ እንደደረሳቸውም አትቷል፡፡”

የዚሁ ስልጠና አካል የሆነ ስልጠና ከነገ ጀምሮ በደቡብ ወሎ ዞን ኩታበር ወረዳ ከየቀበሌው ለተውጣጡ ከ200 በላይ ለሚሆኑ የኢህአዴግ አባላት ለሁለት ቀን ይሰጣል፡፡

ኢህአዴግ በጎንደር የጤና ሰራዊት በሚል በሺ ለሚቆጠሩ አባሎቹ ስልጠና እያሰጠ እንደሆነም ታውቋል። ስልጠናው በአገራችን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ማካተቱንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል። አምና በተካሄደው ተመሳሳይ ስልጠና ኢሳት መታፈን በተሰብሰባዊው ጥያቄ ሆኖ ቀርቦ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።