በወልድያ የታሰሩት ፍርድ አጥተው በመሰቃየት ላይ ናቸው

ነሃሴ ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አንዲት አራስን ጨምሮ ከ19 ያላነሱ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ለአንድ ወር ያክል በእስር ካሳለፉ በሁዋላ ዛሬ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም ምንም መፍትሄ ሳይሰጥ ወደ እስር ቤት እንደሚለሱ ተደርጓል።

የአካባቢው ሰዎች ፍትህ ለማግኘት በፍርድ ቤቱ አካባቢ ቢሰባሰቡም በፖሊስ ሀይል እንዲበተኑ ተድርጓል።

አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ በቂ ማስረጃ ያልቀረበለት በመሆኑ ጉዳያቸውን መከታተል አቁሟል። ኢሳት በነዋሪዎች በኩል የሚቀርበውን አቤቱታ ለማጣራት ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም።

በሌላ ዜና ደግሞ አቶ ተገኘ ሲሳይን ጨምሮ 15 የሳንጃ ወረዳ የአንድነት ፓርቲ አባላት ወደ ማእከላዊ እስር ቤት መዛወራቸው ታውቋል።

15ቱ እስረኖች በጎንደር ከተማ ታስረው ከቆዩ በሁዋላ የፌደራሉ መንግስት ጉዳያቸው ከአገር ደህንነት ጋር የተያያዘ ነው በሚል ወደ ማእከላዊ እስር ቤት እንዲዞሩ አድርጓቸዋል።

አቶ ተገኘ የተከሰሱት በትጥቅ ትግል ለሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ሰዎችን በመመልመልና ግንኙነት በመፍጠር ወንጀል ተከሰው ነው።

እጅግ ከፍተኛ የሆነ ድብደባ የተፈጸመባቸው አቶ ተገኘ በአሁኑ ጊዜ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው አያውቁም።

በተመሳሳይ ዜናም ከደብደረታቦር እና መራዊ ከተሞች ታስረው የተወሰዱት መምህራንና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እጣ ፋንታ እስካሁን አልታወቀም። መንግስት በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ባለመመስረቱ እስረኞቹ ፍትህ አጥተው በመንገላታት ላይ መሆናቸውን ጉዳዩን የሚከታተለው ባልደረባችን ገልጿል።