አቶ መለስ ዜናዊን ለመዘከር በተለያዩ ከተሞች ማእከላት እየተገነቡ ነው

ነሃሴ ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አቶ መለስ ዜናዊን አንደኛ የሙት አመት መታሰቢያ በማድረግ በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች የዝክረ መለስ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ነው። በአዲስ አበባ 100 ሄክታር መሬት ስፋት ያለው ቦታ ከሀያት ሆስፒታል ፊት ለፊት ለመለስ ማእከል ግንባታ ተከልሏል። መስተዳድሩ ማእከሉን እንደሚያሰራ የአዲስ አበባ መስተዳድር አዲሱ ከንቲባ ድሪባ ኩማ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት ገልጸዋል። ግንባታው ምን ያክል ገንዘብ እንደሚፈጅ ግን አቶ ድሪባ የተናገሩት ነገር የለም።

የመለስ ፋውንዴሽን ሰብሳቢ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ የባለራእዩን መለስ ዜናዊ አረንጓዴ ልማት በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚያስኬድ ገልጸዋል።በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችም በመለስ ስም በአደባባዮች ዙሪያ ችግኞች እየተተከሉ ነው።

ኢህአዴግ የአቶ መለስን ሞት ለፓለቲካ ጥቅም ማስገኛ እያዋለነው ነው በሚል ሲተች ቆይቷል።

ከአቶ መለስ ዜናዊ ነባር ጓደኞች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ስብሀት ነጋ በቅርቡ ከኢህአዴግ ልሳናት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ መለስ በንባብና በትምህርት ያገኘውን እውቀት ለህዝብ ለማዋል ቢንቀሳቀስም፣ ፓርቲው ባስቀመጠው መሰረት አለመጓዙን፣ በአገሪቱ ውስጥ ሙስናን በመዋጋት፣ ጠባብነትንና  ትምክህትን በመቅረፍንም በኩል  ድክመት ማሳየቱን ተናግረዋል። መለስ ከሞተ በሁዋላ የፓርቲው ችግር ገሀድ መውጣቱንም አቶ ስብሀት አክለው ገልጸዋል።