ነሃሴ ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የኦሮሚኛ ፕሮግራም ባልደረባ የነበረው ባለቤቷ ጋዜጠኛ ዳበሳ ዋቅጅራ ከሦስት ዓመት እስር በሁዋላ ከአገር መውጣቱን ተከትሎ በኦነግ አባልነት ክስ ተመስርቶባት ታስራ የቆየችው ጋዜጠኛ ሌሊሴ ወዳጆ ከ እስር ተፈታች።
በ 1995 ዓመተ ምህረት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየሠራ ሳለ ድንገት ለእስር የተዳረገው ጋዜጠኛ ዻበሳ ዋቅጅራ አንዳችም ክስ ሳይመሰረትበት ለሦስት ዓመታት በእስር ከቆየ በሁዋላ መፈታቱ ይታወሳል። ከእስር ቢለቀቅም በዙሪያው የነበረው ሁኔታ ለህይወቱ አስጊ መሆኑን የተገነዘበው ጋዜጠኛ ዳበሳ አገሩን ጥሎ የስደት ህይወትን ለመቀላቀል ተገዷል።
ጋዜጠኛ ሌሊሴ ለእስር የተዳረገችው ባለቤቷ ዳበሳ ከአገር መውጣቱን ተከትሎ ነው።
በ ኢትዮጵያ ሚሊኒየም፤ማለትም በ2000 ዓመተ ምህረት ከኦነግ ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶባት የ 10 ዓመት እስራት የተፈረደባት ጋዜጠኛ ሌሊሰ፤ ከሦስት ልጆቿ ተነጥላ ላለፉት ዓምስት ዓመታት በእስር ስትንገላታ ቆይታለች።
ከዓመታት እስር በሁዋላ የተፈታችው ሌሊሴ በ አሁኑ ጊዜ አውስትራሊያ ከሚገኘው ከባለቤቷ ዳበሳ ጋር ተቀላቅላለች።
ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ኮሚቴን(ሲፒጄን) ጨምሮ የተለያዩ የጋዜጠኞች መብት ተቋማትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የ ኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኛ ሌሊሰን እንዲፈታ ሲወተውቱ መቆየታቸው ይታወሳል።