ነሃሴ ፮(ስድስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የሕዝበ ሙስሊሙን ከ18 ወራት በላይ የዘለቀ እንቅስቃሴ በኃይል ለማፈን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ እየወሰደ ያለው እርምጃ በሙስሊም አባላቱ ዘንድ ቅሬታ ማሳደሩ የግንባሩን ከፍተኛ አመራር ስጋት ውስጥ እንደጣለ የውስጥ ምንጮች ጠቆሙ፡፡
አብዛኛዎቹ የግንባሩ ሙስሊም ከፍተኛ የአመራር አባላትን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ መካከለኛ፣ ዝቅተኛ አመራር አባላት መንግስት በሙስሊሙ ጥያቄ አፈታት ጉዳይ እየተከተለ ባለው ኃይል የተቀላቀለበት እርምጃ ደስተኛ ካለመሆናቸውም በላይ በየአጋጣሚውም ቅሬታቸውን መግለጽ መጀመራቸው የግንባሩን ከፍተኛ አመራር አስደንግጧል፡፡
ግንባሩ የሙስሊሙ ድጋፍ አለኝ ለማለት ሙስሊም አባላቱን በጉዳዩ ላይ በማወያየትና ርዕዮት ዓለሙን በስልጠና መልክ በማስረጽ፣ አባላቱ ድርጊቱን እንዲያወግዙ ሲያደርግ ቢቆይም በተግባር ግን ሙከራው የሚፈልገውን ውጤት አላስገኘለትም፡፡በዚህም ምክንያት መንግስት ሙስሊሙን በተመለከተ የሚያስባቸውም ሆነ የሚወስናቸው ጉዳዮች በፍጥነት ሕዝበ ሙስሊሙ ጋር መድረሳቸው ከፍተኛ አመራሩን ይበልጥ ስጋት ውስጥ ጨምሮታል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ሙስሊሙን ጨምሮ የኢህአዴግ ከፍተኛና መካከለኛ አመራርን በተከታታይ ለማሰልጠን ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ያስታወሰው ምንጫችን ሆኖም ስልጠናው በቂ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ በአሁኑ ወቅት ከሙስሊሙ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ይልቅ በውስጡ የተፈጠረው ቅሬታ ይበልጥ ስጋት ውስጥ ሊከተው ችሏል፡፡ ችግሩን ለመፍታትም
በዚህ ወር መጨረሻ ሊካሄድ ከታሰበው የሰላም ኮንፈረንስ በፊት እንደገና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በስፋት ለማካሄድ በመዘጋጀት ላይ ነው፡፡በኢህአዴግ ሙስሊም አባላት የተፈጠረው ቅሬታ አሁን በያዘው መልኩ የሚያድግ ከሆነ ግንባሩ እስከ መሰንጠቅ የሚያደርስ አደጋ ውስጥ ሊከተው እንደሚችልም ምንጫችን ጨምሮ ጠቁሟል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠ/ሚ ሐይለማርያም ደሳለኝ ድምጻችን ይሰማ በማለት የመብት ጥያቄ ባነሱት እና በአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ ገለጸዋል።
የኢህአዴግ ልሳን ከሆነው ዋልታ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ መንግስት ራሱ አክራሪ ብሎ በፈረጃቸው ዜጎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል። ስም ባይጠቅሱም አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችንም አስጠንቅቀዋል።
የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በኢድ አል ፈጥር እለት በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ በወሰዱት እርምጃ 5 ሰዎች ተገድለዋል።