ነሃሴ ፩(አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ ግንባታ በሚል ሰበብ ከዚህ ቀደም እንዲፈርሱ ከተደረጉት ከመስቀል አደባባይ ቃሊቲ የሚዘልቀው መንገድ የመሀል ክፍልና ከደሴ ሆቴል ወደ ፑሽኪን አደባባይ ከተዘረጋው አዲስ ከፊል የአስፓልት መንገድ በተጨማሪ ፣ ከ192 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጐበት ከሾላ ገበያ በለም ሆቴል እስከ አንበሳ ጋራዥ የተገነባው መንገድ የተወሰነ ክፍሉ በቅርቡ እንደሚፈርስ ሪፖርተር ዘግቧል።
ከ20 ዓመታት በላይ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ከሶስት አመታት በፊት የተገነባው ይህ መንገድ በከፊል እንዲፈርስ የተወሰነው፣ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ለሚዘረጋው የባቡር መስመር ለም ሆቴል አካባቢ ሐዲዱን ለሚሻገሩ ተሽከርካሪዎች ማስተላለፊያ መንገድ ለመገንባት ነው ተብሎአል።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት ካደረጋቸውና ከባቡር መስመሩ ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚያፈርሳቸው ለሦስቱ መንገዶች ግንባታ በአጠቃላይ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጓል።
የባለሥልጣኑ የመንገድ ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ዋና የሥራ ሒደት መሪ ኢንጂነር ሙሉጌታ አብርሃም ለጋዜጣው እንደገለጹት፣ ለባቡር መስመሩ ግንባታ ሲባል የፈረሱትና በቅርቡም ይፈርሳሉ የተባሉት መንገዶች ባልተጠበቀው የባቡር ፕሮጀክት ምክንያት ነው፡፡
ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ለደረሰው ኪሳራ ሀላፊነቱን መንግስት መውሰድ እንዳለበት ቢታወቅም፣
ኢንጂነር ሙሉጌታ ግን ‹‹መንገዶቹ ገና በአዲስነታቸው የመፍረሳቸው ዋና ምክንያት ልማቱ ከምንጠብቀው ጊዜ በላይ ፈጥኖ የመጣ በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም፤›› የሚል መልስ ሰጥተዋል።