ሐምሌ ፳፬(ሃያ አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመቃብር ቦታ ጥያቄያችን አልተመለሰም ፤ ለመስጊዶቻችንን የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር ተከልክለናል፡፣ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ፍትህ አጥቷል” በማለት ሙስሊሞች ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ ኗሪ የሆኑት ሐጅ ሙርፉቅ ሙስሊሙ ከመንግስት ጋር ሆድና ጀርባ መሆኑን ገልጸዋል።
በየቀኑ ደብዛቸው እየጠፋ በአፋልጉኝ የሚጠሩት ህዝበ ሙስሊሞች የመንግስት የአፈና ውጤት መሆናቸውን የተናገሩት የጎንደር ህዝበ ሙስሊሞች፤ያለምንም ፍትህ የሚያስረውና የሚያንገላታው ኢህአዴግ የማሰተዳደር አቅሙ ደካማነትን የሚያረጋግጥ የእምነት አፈናው ውጤት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የህዝበ ሙስሊሙን ድምጽ በማፈን ስልጣንን ማቆየት አይቻልም በማለት የተበሳጩ አንዳንድ ወጣቶች ፤ ለዘገባ በሄዱ በአማራ ክልል ጋዜጠኞች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል፡፡
ጋዜጠኞቹ ፤ የረመዳንን ክብረ በዓል ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ቀረጻ ለማድረግ ፤ ቅዳሜ ገበያ ዋናው መስጊድ የሶላት ስርዓትን ለመቅረጽ በተገኙበት ስዓት ነው ጥቃቱ የተሰነዘረባቸው። ” ያለ ፈቃዳችን መንግስት እየቀረጸ ‹‹ ጅሃዳዊ ሃረካት›› የተሰኝ ፊልም ቆርጦ በመቀጠል ለሚያዘጋጀውና ሙስሊሞችን በመወንጀል ለሚተባበር እውነት አልባ ሚዲያ ፤ ልንቀረጽ አይገባም” በማለት ባነሱት ተቃውሞ ፤ በመስል ቀራጩ ወይም ካሜራ ማኑ ላይ አካላዊ ጉዳት አድርሰውበታል ። ካሜራ ማኑ የያዘውን ካሜራም መሬት ላይ ከስክሰውታል። አድማ በታኞች ፖሊሶች በስፍራው ሲደረሱ ወጣቶቹ ሮጠው አምልጠዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ መንግስት ፤ በሚያደርስብን ጭቆና ፤ ከእምነት ተቋማችን እንዲደርስ አንፈልግም ‹‹አላህ ወ አክብር ›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ በመላ ሐገሪቱ እየበረታ መምጣቱን ተከትሎ በመላ ሐገሪቱ ከጅማ ፤ከከሚሴ ፤ደሴ ፤ ወልድያ፤ ቀጥሎ በአራተኛነት ደረጃ ጎንደር በስጋት ቀጠና መንግስት በሐይማኖት አክራሪነት የፈረጃቸው ከተማዎች ናቸው ፡፡