ከ2 ቢሊዩን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገነቡ የውሃ ተቌማት ላይ ጉዳት ደረሰ

ሐምሌ ፳፬(ሃያ አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ዞንና ወረዳዎች በበጎ አድራጊዎች ድጋፍና በህብረተሰቡ የተገነቡ ከ110 በላይ  የውሃ ተቌማት ላይ የእጅ ፓምፕ ዝርፊያ በመፈጸሙ በውሀ አቅርቦቱ ላይ ችግር ተፈጥሯል።

ዝርፊያውን ተከትሎ የወረዳ አመራሮች ለህዝቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው እያሉ ፤ ፓርቲዎችን የማሰጠላት ዘመቻ እያከናወኑ ነው፡፡

በተለያዩ  አካባቢዎች እየተከሰተ ባለው የውሃ ተቋማት ዝርፊያ እስካሁን ወደ 250 የሚጠጉ ሰዎች  ከ2 ወር እስከ 12 ዓመት በእስራት እንዲቀጡ ተደርጓል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በደቡብና ሰሜን ጎንደር ፤ደቡብና ሰሜን ወሎ የእጅ ውሃ ማውጫ ፓምፖች ተሰርቀው ከጥቅም ውጭ ሁነዋል፡፡

የጉዳቱን መጠንና ችግሩን በተመለከተ የክልሉ ውሃ ሃብት ቢሮው ይፋ ያላወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው የችግሩ መጠን መባባሱን ያሳያል፡፡ በዚህ ሂደት ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ወገኖች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የተሞከረ ቢሆንም እስካሁን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋል አልተቻለም፡፡