ሰኔ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና :- በሃገሪቱ የሚገኙ ዋና ዋና የሲምንቶ ፋብሪቻዎች በመብራት ሃይል እጥረት ምክንያት ስራ ለማቆም ወይም ምርታቸውን ለመቀነስ መገደዳቸው ታውቋል።
አቢሲኒያ ፣ ናሽናል፣ ሙገር እና ደርባን ሲምንቶ ፋብሪካዎች በመብራት ችግር ሳቢያ የምርት ሰአታቸውን ከመቀነስ ጀምሮ ለተወሰኑ ቀናት ስራ ማቆም ጀምረዋል። ሌሎች ፋብሪካዎች ደግሞ መብራት ቆጥበው እንዲጠቀሙ የሚያሳስብ ደብዳቤ ከመብራት ሀይል ደርሶአቸዋል። አንዳንድ ፋብሪካዎች ጄኔረተሮችን ለመጠቀም መገደዳቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
መብራት ሀይል የኤልክትሪክ ሀይል ለጅቡቲ መሸጥ መጀመሩ ይፋ መደረጉ ይታወቃል። ሱዳን፣ ኬንያና የመንም እንዲሁ የኤልክትሪክ ሀይል ለመግዛት መስማማታቸው በመንግስት የመገኛ ብዙሀን ይፋ ቢደረግም በአገሪቱ ያውም በክረምት ወራት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የመብራት መጥፋት በተደጋጋሚ መከሰቱ የመንግስትን ፖለሲ ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል ሲል ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ገልጿል።