ሰኔ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሶፊያን አህመድ ለፓርላማው ባቀረቡት የ2006 በጀት መግለጫ ላይ
በቀጣዩ ዓመት አገሪቱ 154 ቢሊየን 903 ሚሊየን 290 ሺህ 899 ብር ረቂቅ በጀት
በሚኒስትሮች ም/ቤት መጽደቁን አመልክተዋል። ይህ በጀት ከአምና ጋር ሲነጻጸር የ12 ነጥብ 3 በመቶ
ብልጫ አለው፡፡
በረቂቅ በጀቱ ድልድል ከተደረገላቸው ተቋማት መካከል መከላከያ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር፣ ፍትህና
ደህንነት 3 ቢሊየን 41 ሚሊየን ብር ለመደበኛና ለካፒታል ወጪ ተመድበውላቸዋል፡፡
መከላከያ እየተጠናቀቀ ባለው የ2005 ዓም በጀት 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ተመድቦለት የነበረ ሲሆን ዘንድሮ በጀቱ በ1 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል።
በተመሳሳይ መልኩ ፍትህና ደህንነት በ2005 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ተመድቦላቸው ነበረ ሲሆን ፣ በ2006 አመት በጀት አሐዙ በ700 ሚሊዮን ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡
በ2006 ዓም ትምህርት በ26 ቢሊዮን ብር ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል።
በቀጣዩ ኣመት ከአገር ውስጥ ገቢ፣ ከመሰረታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ድጋፍ ፣ ከዕዳ ቅነሳ ፣ከፕሮጀክት ብድርና
ዕርዳታ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ገቢ 138 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ሲሆን ከዚህ ከጠቅላላ ገቢ ውስጥ የአገር
ውስጥ ገቢ ድርሻ 77 በመቶ ይደርሳል፡፡ የቀጣዩ ኣመት 154 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በጀት የብር 16 ነጥብ 6
ቢሊየን ብር ጉድለት እንደሚታይበትም ተጠቁሟል፡፡ ይህን የበጀት ጉድለትም ከአገር ውስጥ ባንኮች በሚገኝ ብድር
ለመሸፈን ዕቅድ መያዙን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡