በመተማ የሁለት ቀበሌ ነዋሪዎች በመሬት ዙሪያ ከመንግስት ጋር እየተወዛገቡ ነው

ሰኔ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በመተማ ዮሐንስ እና ኮኪት ቀበሌዎች የሚኖሩ አርሶአደሮች መሬታችን አድሎአዊ በሆነ መልኩ ለባለሀብቶች እየተሰጠብን ነው በማለት ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ነው። የነዋሪዎቹ ተወካይ እንደተናገሩት አቤቱታቸውን ለም/ል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ለአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ጎበዜ ቢያቀርቡም ፣  ባለስልጣኖቹ ” አልሰማንም ” የሚል መልስ ከመስጠት በስተቀር ፣ ለችግራቸው ፈጣን መልስ አልሰጡም።

መንግስት መሬት የአለአግባብ እየተረፈ ነው በሚል  ምክንያት  መሬትን በብሎክ የመከፋፈል አሰራር ተግባራዊ ማድረጉን የገለጡት ተወካዩ ይሁን እንጅ የአካባቢው ባለስልጣናት ለም የሆኑ መሬቶችን ለባለሀብቶች እና ለእነሱ ቀረቤታ ላላቸው ሰዎች በመሰጠታቸው ተቃውሞ መነሳቱን ገልጸዋል ።

በጉዳዩ ዙሪያ የአካባቢውን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። በ

በሌላ ዜና ደግሞ በደቡብ ክልል ዲላ ከተማ ከ3 ቀናት በፊት በተነሳ ቃጠሎ የ66 አባዎራዎች ቤት መቃጠሉን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። የወረዳው ባለስልጣናት “አካባቢው ለልማት ይፈለጋል” በሚል ምክንያት ነዋሪዎቹ ” አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ላለፉት 2 አመታት ሲያሳስቡ ቆይተዋል። አንዳንድ ነዋሪዎች እንደተናገሩት የወረዳው ባለስልጣናት ሆን ብለው ቤታቸውን አቃጥለውባቸዋል። የወረዳው ባለስልጣናት ስለሚቀርብባቸው ወቀሳ አስተያየት አልሰጡም።