ሰኔ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የደቡብ ክልል ርእሰ መዲና ሓዋሳ እና የአማራ ክልል ርእሰ መዲና ባህርዳር የክልል ርእሰ መዲናነታቸውን በማስረከብ በቀጥታ በፌደራል መንግስቱ አንደሚተዳደሩ ታውቋል፡፡
የሚኒስትሮች ም/ቤት ለውይይት ባዘጋጀው ሰነድ ላይ እንደገለጸው ከተሞቹ ከርእሰ መዲናነት ወደ ፌዳራል ከተማነት በመሸጋገር ለማእከላዊ መንግስት ግብር ይከፍላሉ፣ በማእከላዊ መንግስት ይተዳደራሉ።
በአቶ አዲሱ ለገሰ መሪነት የብአዴን ባለስልጣናት ውይይት አድርገዋል። ባህርዳር የክልል ርእሰ መዲናነቱዋን ለደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ደብረ ታቦር ታስረክባለች።
በደቡብ በኩል የክልሉን ዋና ከተማ ለመምረጥ ከፍተኛ ችግር ማጋጠሙ ታውቋል። ክልሎች ወደ ፊድራል ሲዛወሩ ከአዲስ አበባ እና ድሬድዋ ቀጥለው ለፊድራል መንግስቱ የሚገብሩ ተጠሪ ከተሞች ይሆናሉ፡፡
የገቢ አቅማቸው አድጓል በሚል የተወሰነባቸው ከተሞች እጣ ፈንታ በክልሎች የማግባቢያ ውይይት ተደርጎበት 2006 ላይ ተግባራዊ ይሆናል፡፡
በአማራ ክልል የክልል መዲናነቱን የአዊ ዞኖዋ ዳንግላ፤የምዕ/ጎጃሞዋ ፍኖተ ሰላም ፤የምስ/ጎጃሞዋ ደብረ ማርቆስ ፤የወሎዋ ወልድያ ጥያቂያቸውን እንዲሚያነሱ ይጠበቃል፡፡
ከደቡብ ክልልም የወላይታ ሶዶን ከተማ እና አርባ ምንጭን ካፋጠጠው ጉዳይ አንስቶ ስልጤ ፤ጉራጌ፤ ከንባታ እና ሃድያን ቅሬታ ውስጥ ይከታቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አቶ አዲሱ በደቡብ ክልል የታየውን አይነት ብጥብጥ በአማራ ክልል እንዳይደገም ሁላችሁም ደብረታቦርን በዋና ከተማነት ተቀበሉ በማለት ለተሰብሳቢዎች ገልጸዋል።
ከፍተኛ ገቢ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ግብር በመክፈል በ9ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የተወደሰችውን መቀሌ ወደ ፌደራል መንግስቱ ለማዞር እቅድ ይኑር አይኑር አልታወቀም።