የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ በከፍተኛ የአስተዳደር ችግር ውስጥ መግባቱዋን የሀይማኖት አባቶች ገለጹ

ሰኔ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አንዳንድ ካህናት የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች በመሆናቸው ቤተክርስቲያኑዋን እየጎዱዋት ነው ሲሉ የሀይማኖት አባቶች ገልጸዋል

ኢሳት ያነጋገራቸው የተለያዩ ሀይማኖት አባቶች እንደገለጹት በስልጣን ላይ ያሉ አንዳንድ ካህናት መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ትተው የገዢው ፓርቲ ካድሬ በመሆናቸው ፣ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ለሚታየው የአስተዳደር መበላሸት ግንባር ቀደም ተጠያቂ ናቸው።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የሀይማኖት አባት  “በከተማው፣ በገጠሩ በርካታ የሀይማኖት አባቶች በአንድ እጃቸው መስቀል በሌላው  ሽጉጥ ታጥቀው በመዞር አትግደል የሚለውን የእግዚአብሄር ህግ እየጣሱ የገዢው ፓርቲ ካድሬ በመሆን እያገለገሉ ነው” በማለት ተናግረው፣  ችግሩ የቤተክርስቲያኒቷ የአስተዳደር መበላሸት ያመጣው መሆኑንም አክለዋል” ።

በአሁኑ ሰአት ለቤተክርስቲያኑዋ ገዳይ የሆነ በሽታ ዘረኝነት ነው ያሉት የሀይማኖት አባቱ፣ ሙስናም ሌላው ችግር መሆኑንም ገልጸዋል። ዛሬ ዛሬ በቤተ ክህነቱ ሰባቱ ምሥጢራተ

ቤተ ክርስቲያንና አምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ትርጉማቸው ተለውጦ ሰባት ሺና አምስት ሺ ብር ሆነዋል፡፡

‹ከሐዋርያት ጋር ና›. ማለት አሥራ ሁለት ሺ ብር ይዘህ ና፤ ‹ሰባው አርድዕት የሉም ወይ›. ማለት ሰባ ሺ ብር

ያስፈልግሃል፤ ሠላሳ ፣ ስድሳና መቶ ማፍራት ሰለሳ፣ ስድሳና መቶ ሺ ብር መስጠት ሆነዋል፡፡ በማለት ቤተክርስቲያኑ በሙስና መዘፈቁዋን ገልጸዋል።

ሌላ የሀይማኖት አባት ደግሞ ” ቤተክርስቲያኑዋ በአስተዳደር ችግር ምክንያት በከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ በመግባቱዋ እንዲሁም የሀይማኖት ትምህርት የተማሩት ጠንካራ ዘመድ ከሌላቸው ስራ ለማግኘት ስለማይችሉ ቄስ ለመሆን የሚፈልግ ሰው እየጠፋ ነው ብለዋል። መንግስት የቤተክርስቲያኑ ታሪክ እንዲጠፋ፣  ቤተክርስቲያኑ እንድትደክም እያደረገ ነው በማለትም ወቅሰዋል።

በጉዳዩ  ላይ የቤተ ክህነት ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ  አልተሳካም