በእስር ላይ የሚገኘው የባለራእይ ወጣቶች አመራር በህግ አማካሪውና በቤተሰቦቹ እንዳይጎበኝ ተከለከለ

ግንቦት ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ማህበሩ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የባለራእይ ወጣቶች የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆነው ወጣት ብርሀኑ ተክለያሬድ ” ግንቦት27 ፣ 2005 ኣም ከጧቱ ሶስት ሰአት ላይ ሜክሲኮ በሚገኘው ፍርድ ቤት ለ3ኛ ጊዜ ቢቀርብም፣ ጉዳዩ ሳይታይ ቀጠሮ ተጠይቆበት እንደገና ወደ እስር ቤት ተመልሷል።

ማህበሩ አያይዞም ከግንቦት 27 ቀን 2005 ዓም ጀምሮ ወጣት ብርሀኑ በቤተሰቡም ሆነ በጓደኞቹ እንዲሁም በህግ አማካሪው እንዳይጎበኝ መወሰኑን ለማረጋገጥ መቻሉን ጠቅሷል።

ማህበRU ውሳኔው ” በእጅጉ የስርአቱን በአደገኝነት ሁኔታ ገፍቶ መቀጠል የሚያሳይ በመሆኑ የሀገር ውስጥ እና አለማቀፍ ጋዜጠኞች የመብት ተሟጋች ድርጅቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንድተሰጡ እና የሰላማዊ ትግል ጥሪያችንን በንቃት እንድትጠብቁ ” እንጠይቃለን ብሎአል።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርነው የማህበሩ ስራ አስፈጻሚ ወጣት ሀብታሙ አያሌው በትናንትናው እለት በተሰየመው ችሎት ከጠበቃው ከአቶ ተማም አባቡልጉ በስተቀር ሌሎች ሰዎች እንዳይገቡ መደረጉን ገልጾ፣ ፖሊስ በቂ የሆነ ማስረጃ ለማቅረብ ባለመቻሉ እና ለ3ኛ ጊዜ የጊዜ ቀጠሮ በመጠየቁ የአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ተጨማሪ 2 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ መስጠቱን ገልጿል።

ፖሊስ በ 2 ቀናት ውስጥ ክስ መመስረት ካልቻለ ዳኛው ክሱን እንደሚዘጉት ማስታወቃቸውን ከጠበቃው እንደተረዳው ወጣት ሀብታሙ  ገልጿል።

ወጣት ብርሀኑ ከአሁን በሁዋላ ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዳይገናኝ ትእዛዝ ሲተላለፍ መስማቱንም ሀብታሙ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ህገመንግስት በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች በቤተሰቦቻቸው እና በህግ አማካሪዎቻቸውን የመጎብኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።