ግንቦት ፳፬ (ሀያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አሜሪካ ውስጥ በኢዩጂን በተደረገው የዳይመንድ ሊግ አትሌቲክስ ውድድር አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ10ሺህ ሜትር ውድድር በማሸነፍ ወደ ቀድሞ ክብሩ መመለሱ ታወቀ።
በ10 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት፣ እንዲሁም የኦሎምፒክ ሶስት የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ የሆነው ቀነኒሳ በደረሰበት ጉዳት ለረጅም ጊዜ ከውድድር ርቆ መቆየቱ ይታወሳል። ምንም እንኳን ቀነኒሳ ከጉዳቱ በደንብ ሳያገግም ባለፈው የለንደን ኦሎምፒክ ላይ ቢካፈልም ሳይቀናው በተቀናቃኙ እንግሊዛዊ ሞፋራህ ተቀድሞ ነበር ውድድሩን የጨረሰው።
ይኸው በእጅጉ ሲያስቆጨው የነበረው ቀነኒሳ ራሱን አዘጋጅቶ ወደ ቀድሞ ብቃቱ በመመለስ ዛሬ ሞፋራህን ለማሸነፍ ብርቱ ዝግጅት አድርጎ እንደነበር አስቀድሞ ቢነገርም፤ አትሌት ሞፋራህ ግን ሆዴን አሞኛል በማለት ውድድሩ ላይ ሳይካፈል መቅረቱ ታውቋል።
በዚሁ ውድድር ላይ ኢትዮጵያኖቹ አትሌት ኢማና መርጋ እና አትሌት አበራ ኩማ እንደ ቅደም ተከተላቸው 2ኛና ሶስተኛ ሆነው ሲጨርሱ፣ ኬንያዊው ካሮኪ ቢታን አራተኛ፣ ኢትዮጵያዊው ብርሃን ተስፋዬ አምስተኛ ሆነው ውድድሩን ማጠናቀቃቸው ታውቋል።
እንደሚያሸንፉ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው ከነበሩት አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው የቀነኒሳ ታናሽ ወንድም አትሌት ታሪኩ በቀለም 12ኛ ሆኖ ውድድሩን አጠናቋል። ታሪኩ በለንደን ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነ ብርቱ አትሌት ነው።
በዚህ ውድድር 2ኛ የወጣው አትሌት ኢማና መርጋም በተለያዩ ውድድሮች አኩሪ ድል በማስመዝገብ ላይ ያለ ወጣት ኢትዮጵያዊ አትሌት ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊትም በዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተካፍሎ በአስገራሚ ብቃት በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀ ተስፋ የሚጣልበት ድንቅ አትሌት ነው።
ቀነኒሳ የዛሬውን ውድድር የጨረሰው 27 ደቂቃ ከ 12.08 ሰከንድ ሲሆን ከስምንት ዓመት በፊት በርቀቱ ያስመዘገበው የዓለም ክብረወሰንን ደግሞ 26 ደቂቃ 17.53 ሰከንድ የሆነ ጊዜ መሆኑ ይታወሳል በማለት ቅዱስ ሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።