184 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወድቆ ያገኘው ኢትዮጵያዊ ገንዘቡን መለሰ

ግንቦት ፳፬ (ሀያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፅዳት ሰራተኛ የሆነው ወጣት ብርሃኑ ጀምበሬ አይሮፕላን ሲያፀዳ በካኪ ወረቀት ተጠቅልሎ ወድቆ ያገኘውን 184 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለባለቤቱ እንዲመለስ ማድረጉ ታወቋል።

 

ወጣት ብርሃኑ በወቅቱ የተሰማውን ስሜት ሲገልፅ “በመጀመሪያ ገንዘቡን ሳገኝ ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ አይቼ ስለማላውቅ በጣም ደነገጥኩ። በዚህም  የተነሳ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ተጋብቼ ጥቂት ደቂቃዎች በማሰላሰል ካሳለፍኩ በኋላ መጀመሪያ የቅርብ አለቃዬን፤ ክዚያም የጥበቃ ሠራተኛውን በመጥራት ገንዘቡን ለሚመለከተው አካል ልሰጥ ችያለሁ።” ሲል ተናግሯል።

ገንዘቡን በማስረከቤ በርካታ ሰዎች «ጨዋ፣ ጎበዝ » አንዳንዶች ግን «ሕይወትህን መቀየር የሚችል ገንዘብ እንዴት ትመልሳለህ?» እንደሚሉት የተናገረው ወጣት ብርሃኑ « እኔ ግን ያልደከምኩበትን ንብረት ባለመውሰዴ ሁሌም ደስተኛ እንድሆን ያደርገኛል» ብሏል።

 

ገንዘቡ የጠፋባቸው ጋምቢያዊው ባለንብረት ካሉበት ተጠርተው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ 184 ሺህ ዶላሩን ትናንት የተቀበሉ ሲሆን፣ በዚህም ወቅት «ሕይወቴን ያገኘሁ ያህል ተሰምቶኛል» ሲሉ ደስታቸውን መግለፃቸው ታውቋል። ወጣት ብርሃኑ ጀምበሬ ያገኘው ገንዘብ በኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር ከ3 ሚልዮን ብር በላይ ነው። :

ከስምንት ወራት በፊትም በላስ ቬጋስ የታክሲ ሾፈር የሆነው ኢትዮጵያዊው አዳም ወልደማርያም፣ ተሳፋሪ ታክሲው ውስጥ ረስቶት ያገኘውን 250 ሺ የአሜሪካ ዶላር ለባለቤቱ መመለሱ ይታወሳል።