ግንቦት ፳፫ (ሀያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአማራ ክልል ፖሊስ በ9 ወሩ የግምገማ ሪፖርት ላይ እንደገለጸው 19 የዳንጋላ ፖሊሶች እስከነ መሳሪያቸው ተሰውረዋል።
ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደገለጹት ፖሊሶቹ ራሱን ይፋ ያላደረገውን እና በ አዊ ዞን በጃዊ በረሀ በስፋት የሚንቀሳቀሰውን አዲስ ወታደራዊ ሀይል ተቀላቅለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወታደሮቹ እንቅስቃሴያቸውን በማስፋት አንዳንድ መጠነኛ የሚባሉ ጥቃቶችን እየፈጸሙ ነው።
የፖሊስ የጸጥታ ሃይሎችን መጥፋት ተከትሎ ድንጋጤ ውስጥ የገባው መንግስት በዞኑ ከፍተኛ ግምገማ እያካሄደ ነው።
ኢህአዴግ በትጥቅ ትግል እንዲወድቅ አልመው ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅት አባላት ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል ተብሎ የሚጠረጠሩ ባለስልጣናትን ሰበብ በመፍጠር ከስልጣን ለማውረድ ግምገማ መጀመሩን ከቀናት በፊት መዘገባችን ይታወሳል።
በጉዳዩ ዙሪያ የዞኑን ባለስልጣናት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።