ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት ሰማያዊ ፓርቲ ለጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ድጋፋቸውን እየገለፁ ነው

ግንቦት ፳፫ (ሀያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በመጪው እሁድ በሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ከሰማያዊ ፓርቲ ጎን እንደሚቆም አስታውቋል።

<<ሰማያዊ ፓርቲ በሰልፉ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች የኛም ጥያቄዎች ናቸው>> ያለው አንድነት ፓርቲ፤ አባላቱና ደጋፊዎቹ ወደ ሰልፉ በመውጣት ድምጻቸውን ያሰሙ ዘንድ መልእክት አስተላልፏል።

የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ  አቶ ዳንኤል ተፈራ ፤ ፓርቲያቸው -የሰማያዊ ፓርቲን ጥሪ ከልብ የሚደግፍ ከመሆኑም ባሻገር የ አንድነት አባላት ከወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ሆነው ድምጻቸውን ለማሰማት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

የ አንድነት ፓርቲ የውጪ ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት አቶ ተመስገን ዘውዴ በበኩላቸው ፦””ሰማያዊ ፓርቲ ያነሳቸው ጥያቄዎች የአንድነትም ጥያቄዎች ናቸው። ፓርቲያችን በአዲስ አበባ በሚገኙ 23 ወረዳዎች ባሉት ሴሎችና ጽ/ቤቶቹ አማክኝነት የቅስቀሳ ሥራ ጀምሯል” ብለዋል።

ከቀናት በፊት  የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መ.ኢ.አ.ድ) በሰላማዊ ሰልፉ- ከሰማያዊ ፓርቲ ጎን እንደሚቆም ማስታወቁ ይታወሳል።

የመኢአድ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር  አቶ ወንድሙ፣ ድርጅታቸው -ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ አባላቱና ደጋፊዎች እንዲገኙ ጥሪ ከማቅረቡም በላይ  ከፍተኛ የማስተባበር ሥራ እንደሚሰራም ጭምር ነው ያረጋገጡት።

ከፓርቲዎቹ ባሻገር አባላቱ በ እስር ቤት እየተንገላቱ የሚገኙበት የባለራዕይ የወጣቶች ማህበር በበኩሉ ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው ሰልፍ ስኬታማ እንዲሆን  ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ በመግለጽ ነው ለሰልፉ አጋርነቱን ያስታወቀው።

ይህ በ እንዲህ እንዳለ ሰማያዊ ፓርቲ- በመጪው እሁድ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ለሚያካሂደው የተቃውሞ ሠልፍ በተለያዩ መንገዶች እየተደረገ ያለው ቅስቀሳ ተጠናክሮ መቀጠሉን  አስታውቋል።
ከፓርቲው ጽሕፈት ቤት የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ትናንት ሐሙስ ብቻ  5ሺህ የድምጽ መልዕክቶች እና 10 ሺህ የጽሁፍ መልዕክቶች በእጅ ስልክ(በሞባይል) ተላልፈዋል፤30 ሺህ በራሪ ወረቀቶች እና 2 ሺህ ፖስተሮች ተሰራጭተዋል፡፡
ሰው ለሰው የሚደረገው ቅስቀሳ በተቀላጠፈ ሁኔታ እየተካሄደ ሲሆን፤ በቀሪዎቹ ጥቂት ቀናትም ቅስቀሳው በልዩ ልዩ ዘዴዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመልክቷል።
ፓርቲው ባደረገው (ብስለት የተሞላበት) ጥረት -ከአዲስ አበባ መስተዳድር የሰልፍ ፈቃድ ማግኘቱ፣ የተለያዩ ስጋቶችን በመቀነስ የሰልፈኛውን ቁጥር ቀደም ሲል ከተጠበቀው በላይ በእጅጉ እንደሚያንረው ብዙዎች ግምታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ሰልፉ እንደተጠበቀው የሚካሄድ ከሆነ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ 8 ዓመታት ወዲህ በተቃዋሚ ፓርቲ የተደረገ የመጀመሪያው ሰልፍ ይሆናል።
ከረዥም ጊዜ በሁዋላ በሚደረገው በዚህ ሰልፍ እልፎች ወደ አደባባይ በመውጣት ሥነ-ስርዓት በተሞላበት፣በበሰለና በሰለጠነ መንገድ እና እጅግ አስደማሚ በሆነ ሁኔታ ተቃውሟቸውን ያሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል።