ግንቦት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የባለራእይ ወጣቶች ማህበር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆነው ወጣት ብርሀኑ ተክለያሬድ በደህንነቶች ከተወሰደ በሁዋላ በማእከላዊ እስር ቤት መታሰሩን ወንድሙ ሙሉጌታ ተክለያሬድ ለኢሳት ገልጿል።
ሀሙስ እለት ፍርድ ቤት የቀረበው ወጣት ብርሀኑ ከእርሱ ጋር ሌሎች በተመሳሳይ መንገድ የታሰሩ 5 ወጣቶች ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
አምስቱ ወጣቶች እርስ በርስ የማይተዋወቁ እና ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ፍርድ ቤት መሆኑን ወጣት ብርሀኑ መናገሩን ወንድሙ ገልጿል ።
መንግስት ለስልጣኔ ስጋት ይሆናሉ በማለት የሚጠረጥራቸውን ወጣቶች በግንቦት7 ፣ በኦነግ ወይም በኦብነግ ስም በሽብርተኝነት ወንጀል እየከሰሰ እስር ቤት እንደሚያስገባ ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት አመልክቷል።