ግንቦት ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ፋሲለደስ እየተባለ የሚጠራው ጀልባ ከቁንዝላ ወደ ደልጊ 102 ሰዎችን አሳፋሮ ሲጓዝ በመስጠሙ አምስት ሰዎች መሞታቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያና አንድ የጣና ሀይቅ ትራንሰፖርት ሀላፊ ገልጸው፣ የአደጋው መንሰኤም በመጣራት ላይ ነው ብለዋል።
አደጋው የተከሰተው ጀልባው ደልጊ ለመድረስ ከ150 እስከ 170 ሜትር ሲቀረው ነው። የአካባቢው ህዝብ ተረባርቦ አብዛኞቹን ተሳፋሪዎች ለማውጣት እንደቻለ የጣና ሀይቅ ትራንስፖርት ባለስልጣን የሆኑት አቶ በለጠ ፈንቴ ለኢሳት ገልጸዋል።
አደጋው የተፈጠረበትን ምክንያት የተጠየቁት አቶ በለጠ፣ እስካሁን ድረስ ትክክለኛውን መንስኤ ለማወቅ አለመቻሉን ፣ መረጃው ከተጣራ በሁዋላ መግለጫ እንደሚሰጡ ገልጸዋል። ጀልባው ችግር የሌለበት መሆኑን እንዲሁም በአካባቢው ማእበል አለመፈጠሩን አቶ በለጠ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ግን የጀልባዋ ካፒቴን በህይወት የተረፈ ሲሆን ካፒቴኑ ለፖሊስ በሰጠው ቃል ህዝቡ ከጀልባው ላይ ለመውረድ ወደ አንድ አካባቢ በመከማቸቱ የጀልባውን ሚዛን ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲያጋድል በማድረጉ ነው በማለት የሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር ዘመነ አመሸ ለመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ምናልባትም በህይወት የተረፈ ካለ እና ተጨማሪ አስከሬኖችን የማፈላለጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ኮማንደሩ ገልጸዋል።
እንዲህ አይነት አስከፊ አደጋ ሲያጋጥም የመጀመሪያው ነው ያሉት ኮማንደር ዘመነ ፥ ትክክለኛውን መረጃ በማጣራት ምክንያቱን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
መንግስት እንደሚለው የ5 ሰዎችን አስከሬን ማግኘት የተቻለ ሲሆን፣ ቀሪዎቹን 56 የሚጠጉ ሰዎች የማፈላለጉ ስራም ቀጥሏል። የአይን እማኞች ግን የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን እየገለጹ ነው። ኢሳት ትናንት ባቀረበው ሰበር ዜና 10 ሰዎች መሞታቸውን መግለጹ ይታወሳል።