ሰሞኑን በደሴ ከተማ ሩቂያ እየተባለ በሚጠራው አዳራሽ በተደረገው ስብሰባ ህዝቡ ስሜቱን በድፍረት ሲገልጽ ዋለ

ግንቦት ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ስብሰባው ከማንኛውም የድምጽና የምስል ቀረጻ ነጻ እንዲሆን ቢደረግም ኢሳት በደሴ ከተማ ከሚኖሩ ወጣቶች ጋር በመተባበር  ስብሰባውን ለመቅረጽ ችሎአል።

በዚህ ስብሰባ ላይ ከመልካም አስተዳዳር እና ከንግድ ጋር በተያያዘ የከተማዋ ታዋቂ ግለሰቦች እና የተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ትችቶችን እና ምስጋናዎችን አቅርበዋል። አብዛኞቹ ተናገሪዎች በከተማው ፖሊስ ላይ ከፍተኛ ነቀፌታ አሰምተዋል።

መንግስቱ ዘገየ የተባሉ የአማራ ክልል የጠበቆች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት እና የህግ አማካሪ “ለዜጎች ለምን ጥብቅና ቆማችሁ ተብለን የእናቶቻችን ስም እየተጠራ በፖሊሶች ተሰድበናል” ብለዋል::

ሌላው ተናጋሪ አቶ ፈቃዱ አለነ ደግሞ ነዋሪዎች በጠራራ ጸሀይ እንደ ኬንያና ናይጀሪያ እየተዘረፉ መሆኑን ገልጸው የፖሊስ አመራሮች ራሳቸውን ማጥራት አለባቸው ሲሉ አክለዋል።

አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በበኩላቸው “ፖሊስና ህዝብ ከተራራቁ ቆይተዋል፣ ከፖሊስ አዛዡ እስከ ተራው መርማሪ ያለው መዋቅር ችግር አለው፣ ሀብታችን ዋስትና አጥቷል” ብለዋል።

አቶ ዮናስ ከበደ የተባሉ ተናጋሪ ደግሞ በምሽት የከተማው ህዝብ እንደልቡ መጓዝ በማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

ገብረማርያም የተባሉ ነዋሪም  እንዲሁ  ሰው የገደለ ሰው 7 ቀን ታስሮ ሲፈታ ሰው ያልገደ ሰው ደግሞ ደሀ ስለሆነ ብቻ ለ2 ወራት ታስሮ ለመፈታቱ ማስረጃ አለኝ በማለት የፖሊስን አሰራር ነቅፈዋል።

ነዋሪዎቹ በንግዱ ማህበረሰብ ላይ እየደረሱ ያሉ በደሎችንም ዘርዝረው አቅርበዋል። እያሱ ጌታቸው የተባሉ ነዋሪ በከተማ ውስጥ አንድ የንግድ ፈቃድ ሰጪ መስሪያቤት ብቻ ቢኖርም፣ የሚያሽጉት ድርጅቶች ብዛት በርካታ መሆን በመንግስት በኩል የተቀናጀ ስራ አይሰራም ወይ? የሚል ጥያቄ እያስነሳ መሆኑን ገልጸዋል።

ህዝቡ ባነሳቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ስብሰባውን የመሩትን የደሴን ከተማ ከንቲባ  አቶ አለባቸውን ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ሊሳካልን አልቻለም።

የስብሰባውን ሂደት ለመቅረጽ የተባበሩንን የደሴ ከተማ ወጣቶች ለማመስገን እንወዳለን።