ግንቦት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በፌዴራል መንግስት ስር ከሚተዳደሩ 13 ብሔራዊ ፓርኮች አንዱና ዋናው የሆነው የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ
የተመዘገበ ሲሆን ፓርኩ ከመመስረቱ በፊት ጀምሮ ሰፍረው የነበሩ ሰዎችን ከአካባቢው ለማስወጣት ከዚህ ቀደም
የተደረጉ ተደጋጋሚ ጥረቶች አለመሳካታቸውን ተከትሎ ዩኔስኮ በቅርቡ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ታውቋል፡፡
ከዩኔስኮ ማስጠንቀቂያ የደረሰው የኢትዮጵያ መንግስት በፓርኩ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከ300 በላይ አባወራዎችን
ለማስወጣት ጥረት መጀመሩን ተከትሎ ከአንድ ሳምንት በፊት ባልታወቀ ሁኔታ በፓርኩ ውስጥ ቃጠሎ ተነስቷል፡፡
ቃጠሎውን ማን እንዳስነሳው ለጊዜው ባይታወቅም በመንግስት በኩል የቃጠሎው መንስኤ የአካባቢው ሰዎች እንደሆኑ የሚገለጽ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ እኛን ከፓርኩ ለማባረር ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ ነው በማለት በቃጠሎው እጃቸው እንደሌለበት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
በአሁኑ ሰዓት በመንግስታዊው የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን በኩል አርቲስት ቻቺ ታደሰ የሚፈናቀሉት
ነዋሪዎች በዘላቂነት ለማቋቋም የገቢ ማሰባሰብ ስራ እንድታከናውን የክብር አምባሳደር ተብላ መሾሟን ምንጮቹ
ጠቁመዋል፡፡
በሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት የሚገኙ ዋልያዎች ቁጥር አንድ ሺ እንደማይሞላና፣ የቀይ ቀበሮ ቁጥርም
ከ300 በታች መሆኑ የፓርኩን ቀጣይ ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል።
በፓርኩ ውስጥ የቤት እንስሳትን ከቀይ ቀበሮና ከዋልያ ጋር ተደባልቀው ማየት የተለመደ ሲሆን
ቀይ ቀበሮዎች ከውሾች ጋር ከመዳቀላቸውም በተጨማሪ በእብድ ውሻ በሸታ በመለከፍ እያለቁ መሆናቸው ለቁጥራቸው
ማሸቆልቆል ትልቅ አስተዋጽዖ እያደረገ ይገኛል፡፡
የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ ከሚገኙ ዋልያና ቀይቀበሮ እንስሳት በተጨማሪ መልክአምድራዊ አቀማመጡን ልዩ
ውበት የሚሰጠው ትልቁ የራስዳሸን ተራራ የሚገኝበት የቱሪስት መስህብ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡