በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት ዳይሬክተር በርሳቸው ጥፋት ቤተሰቦቼ መታሰራቸው አግባብ አይደለም “ሀገሪቱ ምን አይነት ገር እየሆነች ነው” ሲሉ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቀረቡ

ግንቦት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አቶ ገብረዋሕድ ወ/ጊዮርጊስ የጉምሩክ ባለሥልጣን ም/ዳይሬክተር ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው የሚባሉት ባለቤታቸው ኮ/ል ሃይማኖት ተስፋይ መታሰራቸውና ልጃቸውም መደገማቸው ፈጽሞ አግባብ አይደለም ካሉ በኋላ እኔ በጥፋቴ ልጠየቅ ቤተሰቦቼ ለምን? ምን አይነት ሀገር እየሆንን ነው በማለት ታላንት ከሰዓት ባስቻለው ችሎት ጠይቀዋል።

የአቶ ገብረዋሕድ ወ/ጊዮርጊስ ባለቤት ኮ/ል ሃይማኖት ተስፋይ እናታቸው ወ/ሮ ንግሥቲና ልጃቸው አቶ ሃብቶም ገብረመድሕን የታሰሩት ሰነድ አሸሽተዋል በሚል መሆኑን ዐቃቤ-ሕግ በክስ ማመልከቻው ላይ አብራርቷል።

አቶ ገብረዋሕድ የጠየቁትን ግምት ውስጥ በማስገባት ጠበቃቸው የአቶ ገብረዋሕድ ባለቤት ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋይ፣ እህታቸው ወ/ሮ ንግሥቲና ልጃቸው አቶ ሃብቶም በሙስና ስላልተከሰሱ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ይሁንና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን መርማሪዎች ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢወጡ ካላቸው ከፍተኛ ሥልጣንና የገንዘብ አቅም አንፃር ሰነድ ሊያሸሹ ምስክር ሊያባብሉና ሊያስፈራሩ ስለሚችሉ ዋስትና እንዳይሰጣቸው ሲል ተከራክሯል።

ፍርድ ቤቱ መርማሪዎቹን ሰነድ እንዳያሸሹ እንጂ ሌሎች ከተጠረጠሩትበት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑና አለመሆኑ እንዲያስረዱ የጠየቀ ሲሆን፣ መርማሪዎች በተለይ ኮ/ል ሃይማኖት ካላቸው ተሰሚነት አንፃር ሰነድ ሊያስጠፉባቸው እንደሚችሉ አስረድተዋል። ድርጊታቸውም ከሙስና ጋር የተያያዘ በመሆኑ መለቀቃቸውን እንደሚቃወም ተናግረዋል።ኮ/ል ሃይማኖት ሰብአዊ መብታቸውን በሚጋፋ ሁኔታ ራቁታቸውን ሆነው ወደላይ ከፍ ብለው እንዲዘሉ እየተደረጉ መፈተሻቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል። በተፃራሪው መርማሪዎቹ ሁሉም እስረኞች በአግባቡ መበርበራቸውን አስረድተዋል።

የጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አተመላኩ ፈንታ መንግሥት የሚያውቀው በሽታ ስላለባቸውና የሕክምና ክትትል ስለሚያደርጉ እንዲሁም ያለመከሰስ መብት ያላቸው መሆኑን በመግለፅ በዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ያለመከሰስ መብታቸውን በተመለከተ በማስረጃ አስደግፈው እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ያዘዘ ሲሆን ሕክምናን አስመልክቶ ለቀረበው ጥያቄ ዐቃቤ-ሕግ በማረሚያ ቤት በቂ ሕክምና መኖሩን ከዚያም ካለፈ ፖሊስ ሆስፒታል እየተመላለሱ መታከም እንደሚችሉ ለፍድር ቤቱ አስረድቷል።

ሁሉም ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ያደረገው ፍርድ ቤቱ መርማሪዎች የጠየቁትን የ14 ቀን ተጨማሪ ተጨማሪ ቀጠሮ በመፍቀድ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ግንቦት 19 ቀን፣ 2005 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።