በተያያዘ ዜና በጉምሩክ ባለሥልጣኖችና ባለሃብቶች ላይ የተጀመረው የምርመራ ሥራና ዘመቻ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትዕዛዝና መመሪያ መሆኑ ተገለጠ

ግንቦት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑትን አቶ ዓሊ ሱሌይማንን ጠቅሶ ሪፖርተር እንደዘገበው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕይወት በነበሩበት ወቅት በሰጡት የሥራ መመሪያ መሰረት ጥናትተደርጎ የተከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአመት ከአሥር ወር በፊት የሥራ መመሪያ መስጠታቸውን ለተወካዮች ምክር ቤት የተናገሩት ኮሚሽነሩ ጥናቱ ሲጠናቀቅ አቶ መለስ በመታመማቸው ውሳኔ አግኝቶ ወደሥራ ሳይገባ ቆይቷል ብለዋል።በኢትዮጵያ ባለው አሰራር ግማሹ ግብር ይከፍላል፣ ግማሹ ግብር አይከፍልም፣ ግማሹ ታክስ ከፍሎ ዕቃ ያስገባል፣ ግማሹ ታክስ ሳይከፍል ዕቃ ያስገባል ሲሉ ለም/ቤቱ የገለፁት ኮሚሽነር ዓሊ ሱሌይማን፣ በዚህ ምክንያት በንግዱ ኅብረተሰብ ውስጥ ሚዛናዊና የተደላደለ ውድድር እንዳይኖር ማድረጉን አብራርተዋል።

በጉምሩክ የሙስና ተግባር ተጠርጥረው ከታሰሩት መካከል ማንም ሰው ያለመከሰስ መብት ያለው አይመስለኝም ያሉት አቶ ዓሊ፣ ያለመከሰስ መብት ደግሞ ሊነሳ ይችላል ሲሉ አብራርተዋል።

አቶ መላኩ ፈንታ የብአዴንና የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ፣ ከባሕር ዳር ከተማ አዲስ አበባ ለመግባት አየር ላይ እያሉ የአማራ ም/ቤት ያለመከሰስ መብታቸውን ማንሳቱን ለማወቅ ተችሏል፡;

በገምሩክ ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ላይ የተደገረው ምርመራና ክስ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መታዘዙ ሲገለፅ በአቶ መለስ ሞት ማግስት የተሾሙት ጄኔራሎችም በአቶ መለስ እንዲሾሙ የተመለመሉ ናቸው መባሉን በማስታወስ የገዢው ፓርቲ የሚሰራቸውን ሥራ ሁሉ በሞት ከተለዩት የድርጅቱ መሪ ጋር ማያያዝ አስገራሚነቱን ያጎላዋል የሚሉ በዝተዋል።