ሚያዚያ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በክብረ መንግስት ከተማ ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች ” የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ባለስልጣናት ከአካባቢው ደላሎች ጋር በመመሳጠር በእየለቱ በትላለቅ መኪኖች ጣውላዎችን እየጫኑ እንደሚያጓጉዙ” ገልጸዋል። ዛፎችን መቁረጥ እና ከክልል ክልል ማስተላለፍ ህገወጥ ቢሆንም የመከላከያ ባለስልጣናት ግን በዚሁ ንግድ ግንባር ቀደም ተዋናዮች ሆነዋል ብለዋል ነዋሪዎቹ። የመከላከያ መኪኖች በመንገድ ላይ የማይፈተሹ በመሆኑ ፣ ባለስልጣናቱ ጣውላዎችን እየጫኑ ወደ ሰሜን የሚያግዙት በእነዚህ መኪኖች መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ደኖች እየተጨፈጨፉ፣ አካባቢው እየተራቆተ ነው የሚሉት ቧንቧ በሚባል አካባቢ የሚኖሩ አንድ ግለሰብ፣ የመከላከያ ባለስልጣናቱን ደፍሮ የሚጠይቅ ባለመኖሩ፣ ህዝቡ ከንፈር ከመምጠጥ ውጭ የሚያደርገው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
አንድ ሌላ አይን እማኝ የታዘቡትን ለኢሳት ሲገልጹ ደግሞ ” በቅርቡ አንደኛው የመከላከያ መኪና የጥይት ሳጥኖችን አውርዶ ጣውላዎችን ሲጭን የአካባቢው ወጣቶች በንዴት ሳጥኖቹን ይዘው በመጥፋታቸው አራት ሰዎች ተይዘው ሊረሸኑ ሲሉ ሌሎች ሰዎች ሳጥኖቹን እንዳስረከቡና ልጆቹ ከሞት እንደተረፉ ” ተናግረዋል። የደን ጭፍጨፋው በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ አካባቢው ሙሉ በሙሉ ወደ ምድረ በረሀነት ሊለወጥ እንደሚችል እነዚህ ሰዎች አስጠንቅቀዋል።
በሻኪሶ አካባቢ የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት ባለስልጣናት ታንታለም የተባለውን ማእድን በህገወጥ መንገድ ከአገር በማስወጣት ከፍተኛ ገንዘብ እየዘረፉ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።
መንግስት እስካሁን ድረስ ምንም አይነት እርምጃ ለመውሰድ ጥረት ሲያደርግ አልታየም።
በጉዳዩ ዙሪያ የመከላከያ ሰራዊት ባለስልጣናትን አስተያየት ለማግኘት ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።