መጋቢት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኬንቲቻ ቦረና የኢትዮጵያ ማእድን ልማት አክሲዮን ማህበር የተባለ መንግስታዊ ድርጅት ከአመታት በፊት በጉጂ ዞን በሻኪሶና አናሶራ ወረዳዎች 2ሺ 500 ቶን የሚጠጋ ንጹህ የታንታለም ማእድን ማግኘቱ የመገናኛ ብዙህንን ትኩረት ስቦ ነበር።
ኩባንያው ምንም አይነት የማጣሪያ ስራ ሳይሰራ ይህን ውድና ስትራቴጂክ ማእድን በርካሽ ዋጋ መሸጡ አገሪቱን እንደሚጎዳ የዘርፉ ባለሙያዎች ለሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደጋግመው አቤቱታቸውን በማቅረብ ፣ ጥሬ እቃውን ወደ ውጭ መላኩ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
መንግስት በወቅቱ እገዳውን ሲጥል የሰጠው ምክንያት ማእድኑን በዘመናዊ ዘዴ በማምረት የተሻለ ዋጋ ለማግኘት እንዲሁም ከማእድኑ ጋር አብሮ የሚገኘው ዩራኒየም የሚያወጣው ሬዲዮ አክቲቭ ጨረር ለጤና ጠንቅ በመሆኑ የተሻለ አያያዝ ለመፍጠር የሚል ነበር።
እገዳው መንግስት የታንታለም ማጣሪያ ማሽን እስከሚገነባበት ጊዜ ድረስ እንደሚቀጥል በወቅቱ መጠቀሱ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በየአመቱ የምታመርተው ምርት የአለምን ገበያ 20 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን፣ እገዳውም በአለም የታንታለም ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳርፎ ቆይቷል። ዶድ ፍራንክ የተባለው ህግ ኩባንያዎች ግጭት ባለባቸው አገሮች ማእድኖችን ሲገዙ ማእድኖቹ ከግጭቶች ጋር የተያያዙ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ስለሚልና በአለም ላይ አብዛኛውን የታንታለም ማእድን የምታመርተው በጦርነት የምትታመሰዋ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በመሆኗ ኢትዮጵያ በማእድን መላኩ ላይ የጣለችው እገዳ በአለም የታንታለም ገበያ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።
ታንታለም ሊተካ የማይችል እጅግ ውድ የሆነ ማእድን ሲሆን፣ የሞባይል ስልኮችን፣ ኮምፒዩተሮችን እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ፣ ለተለያዩ የኬሚካልና የፋርማሲዩቲካል ውጤቶች መስሪያ፣ ለኤሮስፔስ፣ ለኢነርጂና ባልስቲክ ምርቶች በግባትነት ያገለግላል።
የኢትዮጵያ መንግስት ይህን በአንድ በኩል ውድ ፣ አላቂና ስትራቲጀክ በሌላ በኩል ደግሞ ለጤና አደገኛ የሆነውን ማእድን ወደ ውጭ የመላኩ ስራ ለጊዜው እንዲገታ ቢያደርግም፣ ይህን እገዳ ተጠቅመው የህወሀት ጄኔራሎች ከአንዳንድ ማእድኑን በማውጣት እውቀቱ ካላቸው ቻይናዎች ጋር በመመሳጠር ማእድኑን በመከላከያ መኪናዎች እየጫኑ ፣ አሽዋ ነው በማስባል በሶማሊላንድ በኩል ወደ ውጭ ሲያሻግሩ መቆየታቸውና በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት መዝረፋቸውን በኩባንያው ውስጥ የሚሰሩ ምንጮቻችን ገልጸዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ኩባንያ በአካባቢው የመንገድ ስራ ተቋራጭ በመሆን መንገድ እየሰራ ሲሆን፣ ለመንገድ ስራ ተብለው የተመደቡት መኪኖች ከመንገድ ስራ ይልቅ የታንታለም ማእድንን እየዘረፉ በሶማሊላንድ በኩል ሲያሻግሩ መቆየታቸውን ሰራተኞች ተናግረዋል።
በቅርቡ ደግሞ መንግስት ከፍተኛ የገንዘብ ጥረት ያጋጠመው መሆኑን ተከትሎ ፣ የማእድን ማውጣቱን እና መላኩን እንደገና ለመጀመር በመወሰኑ እነዚህ የህወሀት ጄኔራሎች ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር አክሲዎን በመመስረት ታንታለም በጅቡቲ በኩል መላክ መጀመራቸውን ሰራተኞች አስረድተዋል።
ሰራተኞች ” ይህ ማእድን እያለቀ ነው፣ ታንታለም ስትራቴጅ ማእድን ነው፣ ማእድኑ አሁን ካለቀ አገሪቱ ለወደፊቱ ከፍተኛ የሆነ ገቢ ታጣለች በማለት ሰራተኞች” ገልዋጸዋል።
የሀወሀት ጄኔራሎች ዝርፊያውን የሚፈጽሙት ከዞን ባለስልጣናት ጋር በመዛመድ መሆኑን መንጮች ገልጸዋል።
ምንም እንኳ ኢሳት በአካባቢው ያሉ ተወካዮችን ለማረጋገጥ ባይችልም፣ በህገወጥ መንገድ ከሚወጣው ማእድን ጨረር ጋር በተያያዘ በርካታ የአካባቢው ሰዎች መሞታቸውን ሰራተኞች ገልጸዋል።
መንግስት እገዳው ከመጣሉ በፊት 80 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ታንታለም የሚሸጠው ቻይና ውስጥ ነበር።
በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።
የህወሀት ጄኔራሎች በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ዘመናዊ ህንጻዎች እና የንግድ ድርጅቶችን ሰርተው እንደሚገኙ ኢሳት በማስራጃ አስደግፎ ማቅረቡ ይታወሳል።