መንግስት እና ነጋዴው በዶላር አቅርቦት ዙሪያ ያላቸው ውዝግብ ጨምሯል

መጋቢት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:- በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ከፍተኛ የዶላር እጥረት ተከትሎ ነጋዴዎች ላለፉት 8 ወራት ኤልሲ ከፍተው እቃዎችን ለማስገባት ሳይችሉ ከመቅረታቸውም በተጨማሪ አብዛኛው የውጭ ምንዛሬ መንግስት ለሚያስገነባቸው ግንባታዎች አቅርቦት መግዢያ ብቻ እንዲፈቀድ አድርጎ ቆይቷል።

ሰሞኑን መንግስት ለነጋዴዎች ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት ማንም በውጭ ንግድ ላይ የተሳተፈ ሁሉ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚችል ግልጽ አድርጓል። ይሁን እንጅ አዲሱ መመሪያ ከቀድሞው የሚለይ ሲሆን፣ በዚህ መመሪያ መሰረት የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ ነጋዴዎች በቅድሚያ የጠየቁትን ያክል ገንዘብ በብር ለባንኮች ማቅረብ አለባቸው።

አንድ ነጋዴ 100 ሺ ዶላር የሚጠይቅ ከሆነ ነጋዴው በአገሪቱ የዶላር ዋጋ መሰረት ተመንዝሮ ተመጣጣኝ የሆነውን ብር ማስያዝ ግዴታ አለበት። ይህን አዲስ አሰራር ነጋዴው ሊቀበለው እንዳልቻለ በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ገለጸዋል።

አንድ ነጋዴ ለኢሳት እንደገለጡት መንግስት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት ያጋጠመው በመሆኑ ይህን አዲስ አሰራር ለመዘርጋት ተገዷል። “ነጋዴዎች ዶላር ለማግኘት ሲሉ  በቅድሚያ ብር በባንክ ካስገቡ በሁዋላ፣ መንግስት ዶላሩን በተፈለገው ጊዜ እና ሰአት ባይሰጥና ገንዘቡ ቢበላ ማንነው ሀላፊነቱን የሚወስደው?'” በማለት የጠየቁት ባለሀብቱ ፣ በነጋዴውና በመንግስት መካከል ያለው አለመተማመን ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንም ተናግረዋል።

ኢህአዴግ ሰሞኑን በካሄደው ጉባኤ ከፍተኛ  የአምስት አመቱን የልማት እቅድ ለማሳካት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመው መግለጹ ይታወሳል።

በጉዳዩ ዙሪያ አንድ አስተያየታቸውን የሰጡ ግለሰብ ” መንግስት የገንዘብ እጥረት ቢያጋጥመው አይገርምም፣ ከአቶ መለስ ሞት በሁዋላ የወጡ ወጪዎችን ብናይ ፣ ይህች ደሀ አገር  ያለአቅሟ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ  አውጥታለች። በመጀመሪያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀብር ማስፈጸሚያ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጪ ተደረገ፣ በመቀጠልም የብሄር በሄረሰቦች በአል ለማክበር ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆነ፣ እንደገና የመከላከያ ቀንን ለማክበር በመቶ ሚሊዮኖች ወጪ አደረገ፣ አሁን ደግሞ ኢህአዴግ ጉባኤን ለማካሄድ እንዲሁ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ተደረገ፣ በዚህ ሳምንት ደግሞ የአባይን ግድብ ሁለተኛ አመት ለማክበር እንዲሁ ከፍተኛ ገንዘብ ይወጣል ። በስብሰባ፣ በጉባኤ እየተባለ የሚወጣው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ነው። በዚህም የተነሳ የገንዘብ እጥረት ቢገጥም የሚገርም ሊሆን አይገባም ” ብለዋል።