መንግስት ለአባይ ግድብ ግንባታ ከህዝብ ለመሰብሰብ ያወጣውን እቅድ ሳይተወው አይቀርም ተባለ

 መጋቢት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግስት የአባይ ግድብን በሕዝብ ተሳትፎ ለመገንባት ባቀደው መሰረት ከመንግስት ሰራተኞች፣ባለሃብቶች፣አርሶአደሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እያካሄደ ያለውን የገንዘብ ማሰባሰብ ሒደት ዘንድሮም ለመቀጠልም አቅዶ ቢንቀሳቀስም ከህዝቡ የታሰበውን ያህል ምላሽ ባለመገኘቱ ለማቋረጥ ሳይገደድ እንደማይቀር ምንጮቻችን ገለጡ።

የአባይ ግድብ ከተጀመረ በኋላ በተለይ ባለፈው ዓመት የመንግስት ሰራተኞች ሳይወዱ በግድ የአንድ ወር እና ከዚያ በላይ ደመወዛቸውን በአንድ ዓመት ከፍለው ለመጨረስ ቃል እንዲገቡ በማድረግ ገንዘብ ለማሰባሰብ መሞከሩ የሚታወስ ሲሆን፣  መዋጮው ስጦታ መሆኑ ቀርቶ በቦንድ ግዥ እንደሚያዝ፣ይህም የቁጠባ ባህልን ለማበረታታት ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን በመጥቀስ መንግስት ዘንድሮም መዋጮ ለማሰባሰብ ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ምላ ሹ ጥሩ ባለመሆኑ ምክንያት ለማቋረጥ ሳይገደድ አይቀርም።

ለዚህ አንዱና ዋንኛው ምክንያት ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ ደመወዝተኛው በገቢው ለመተዳደር ያለመቻል ሲሆን በተጨማሪም ለፕሮጀክቱ ከሕዝብ በመዋጮ መልክ የሚሰበሰበው ገንዘብ በምን መልኩ ስራ ላይ እየዋለ እንደሆነ፣ከሙስናና ብልሹ አሰራር የጸዳ ስለመሆኑ ምንም ዓይነት ግልጽ መረጃ አለመኖሩ በሕዝብ ውስጥ ጥርጣሬን ፈጥሯል፡፡  ሌላው ቀርቶ ስንት ብር እንደተዋጣ እንኳን መንግስት ተከታታይነት ያለው በቂ መረጃ እየሰጠ አለመሆኑ የበርካታ ወገኖችን ቅሬታ አስከትሏል፡፡

ለግድቡ ገንዘብ ለመስጠት ቃል የገቡ ሼህ አላሙዲንን ጨምሮ በርካታ ባለሃብቶችም ገንዘቡን በወቅቱ ገቢ አለማድረጋቸው በእነአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና አቶ በረከት ስምኦን የሚመራውን የአባይ ግድብ ብሔራዊ ም/ቤትና አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናትን ማበሳጨቱ ታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከመጋቢት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ሁለተኛ ዓመት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ነው፡፡

 

ከነዚህ ዝግጅቶች መካክል የስነጹሑፍ ፣የስዕል፣የሙዚቃ ዝግጅቶች፣ልዩ ልዩ የአትሌቲክ ውድድሮች፣በተዋናዮችና በድምጻዊያን መካከል መጋቢት 21 በሚካሄድ የእግር ኳስ ውድድር እንዲሁም ግንባታው በሚካሄድበት ቦታ መጋቢት 24 ቀን በሚካሄድ በዓል እንደሚከበር የወጣው መርሃግብር ያሳያል፡፡

 

ግድቡ በአሁኑ ወቅት 18 በመቶ ስራው መጠናቀቁ በመገለጽ ላይ የሚገኝ ሲሆን በስራው ላይ በህወሃት የቀድሞ ታጋዮች የሚመራውና ከተመሰረተ የሁለት ዓመት ዕድሜ ብቻ ያለው የብረታብረት ኮርፖሬሽንን ጨምሮ የኢህአዴግ ኢንዶውመንት ድርጅት የሆነው መስፍን ኢንዱስትሪያል በልዩ ድጋፍ በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ያለው ስራ እንዲያንቀሳቅሱ እየተደረገ ነው፡፡፡ የወ/ሮ አዜብ የእህት ልጅ በሆኑት በወ/ሮ አቲኮ ስዩም አምባየ የሚመራው ኦርቺድ ድርጅትም በግድቡ ስራ ከሳሊኒ በመቀጠል ከፍተኛ ገንዘብ በማግበስበስ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው።

 

ግድቡ በተፋሰሰ አገራት በተለይም በግብጽና ሱዳን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የማያስከትል መሆኑን ለማረጋገጥ የተቋቋመውና በስራ ላይ የሚገኘው የዓለምአቀፍ የኤክስፐርቶች ቡድን በግንቦት ወር 2005 የመጀመሪያ የጥናት ሪፖርቱን ይፋ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ምናልባት የጥናቱ ግኝት እነ ግብጽን የማይጠቅም ከሆነ የግድቡ ግንባታ የመቀጠሉ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚወድቅ እንደሚሆን ተገምቷል፡፡

 

የኢትዮጵያ መንግስት ግን ጥናቱ ግድቡ በተለይ የኢንቫይሮመንት ተጽዕኖ እንደማያስከትል ማረጋገጫ ይሰጥልኛል ብሎ ተስፋ ያደረገ ሲሆን ይህ ባይሆንም እንኳን ግድቡን ከመገንባት የሚያግደኝ የለም እያለ ነው፡፡