ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለው ከሚጓዙት ሰዎች መካከል 2 ህጻናት ታፍነው ሞቱ

መጋቢት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-በዛሬው እለት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ  ክልል በሀይል ተፈናቅለው ወደ ክልላቸው በመጓዝ ላይ ከነበሩት የአማራ ተወላጆች መካከል ሁለት ህጻናት ታፍነው መሞታቸውን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የአካባቢው ነዋሪ  ለኢሳት ገልጸዋል።

እያንዳንዳቸው ከ70 እስከ 80 የሚደርሱ የአማራ ተወላጆችን የጫኑ 6 አይሱዙ መኪኖች ወደ አማራ ክልል የተጓዙ ሲሆን፣ ሁለቱ ህጻናት በመንገድ ላይ የሞቱት አየር አጥሯቸው ነው። እናታቸው ልጆቿን አልቅሳ በወጉ ሳትቀብር በረሀ ላይ እንዲጣሉ መደረጉን  ነዋሪው ገልጸዋል።

በሌላ መኪና የተሳፈረች አንድ ሌላ ህጻንም እንዲሁ አየር አጥሯት ስትደክም ፣ ሾፌሩ አቁሞ ህክምና እንድታገኝ አድርጓል።

አካባቢውን እንዲለቁ ከተጠየቁት መካከል ሁለት ሰዎች ታርደው መገኘታቸውን ግለሰቡ ገልጸዋል።

ከሁለት ቀን በፊት በቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ 60 የአማራ ተወላጆችን  ይዞ ሲጓዝ የነበረ አይሱዙ መኪና ተገልብጦ 59 ሰዎች መሞታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። የአማራ ክልል ተወካዮች ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ማድረግ መጀመራቸውንም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ሰው ገልጸዋል።