መጋቢት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከአካባቢው ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው አደጋው የተፈጠረው፣ ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው መኪና ትክሻ በምትባል ቀበሌ ውስጥ ጀዴሳ በሚባል ወንዝ ውስጥ ገብቶ ነው።
ከትናንት ወዲያ በተፈጠረው አሰቃቂ አደጋ ለሞቱት ሰዎች የደረሰላቸው ሰው አለመኖሩን ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገልጽ የፈለጉ ተፈናቃይ አርሶደሮች ተናግረዋል።
ከሞቱት መካከል ህጻናትና ሴቶችም ይገኙበታል። በአደጋው ዙሪያ የክልሉን ባለስልጣናት ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።
በተመሳሳይ ዜናም በዛሬው እለት በርካታ አርሶ አደሮች በክልሉ ልዩ ሚሊሺያ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
የክልሉ ባለስልጣናት የሚፈናቀሉት ሰዎች በህገወጥ መንገድ ወደ ክልሉ የገቡ ናቸው ሲሉ ለአዲስ አድማስ መናገራቸው ይታወሳል።
የዜጐች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብትን በተለከተ አስተያየታቸውን የሰቱት የሕግ ባለሞያ አቶ ግዛው ለገሠ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 32 “የመዘዋወር ነፃነት” በሚል ርእስ ስር ‹‹ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ አገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ፤ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመኖርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት መብት እንዳለው መደንገጉን ለጋዜጣው ገልጸዋል።