ኢህአዴግ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ

መጋቢት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-በባህርዳር የተካሄደው 9ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን ድርጅቱን በሚቀጥሉት 5 አመታት እንዲመሩ መርጧቸዋል። የብአዴኑ ሊቀመንበርና የትምህርት ሚንስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።
ኢህአዴግ በዚህ ጉባኤ የአመራር ችግር እንደገጠመው በተለይም አመራሩና አባላቱ ተነሳሽነታቸው መቀነሱን ይፋ አድርጓል። ትግሉን ወደፊት ለማስቀጠለም አባላቱና አመራሩ የተከፈለውን መስዋትነት ልብ ሊሉት እንደሚገባ መክሯል። በአገሪቱ ውስጥ የመልካም አስተዳዳር እጦት መስፈኑንና የ5 አመቱን የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድን ለማስቀጠል የፋይናንስ ችግር እንዳጋጠመው ጉባኤው መተማመን ላይ ደርሷል።
በተያያዘ ዜናም ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ከኢህአዴግ አመራርነት ተሰናብተዋል።
በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳዳር የሆኑት ወ/ሮ ገነት ዘውዴ በእድሜ መግፋት በሚል ምክንያት ከኢህአዴግ አመራርነት በዛሬው እለት በይፋ ተገለዋል። ወ/ሮ ገነት የተገለሉት የኢህአዴግ አማራሮች እድሜ እድሜ ከ65 በላይ መሆን የለበትም በሚለው መርህ መሰረት ነው ተብሎአል።
ወ/ሮ ገነት በኢትዮጵያ ውስጥ የትምህርት ጥራት እንዲወድቅ በማድረግ ፣ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ የጸጥታ ሀይሎች እርምጃዎች ሲወስዱ ለማስቆም ባለመቻላቸው ይተቻሉ።
በኢህአዴግ መመሪያ መሰረት 65 ዓመት በላይ የሆነ ሰው ጡረታ ይወጣል፡፡አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ጊዜ መመሪያው በአቶ በረከት ይፋ ሲደረግ እነሱ ሲያረጁ ነው ወይ የዚህ ዓይነት መመሪያ የሚያወጡት የሚል ጥያቄ አስነስቶ ነበር፡፡