መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስአበባ እና በክልሎች የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ምስሎች በክብር እንዲወርዱ አቶ አዲሱ ለገሰ
በመገናኛ ብዙሃን ያስተላለፉት ተማጽኖ እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም።
በቀድሞ የህወሃት ታጋይ ባለቤትነት የሚመራው ሪፖርተር ጋዜጣ የአቶ መለስ ምስሎች ጸሐይና ቁር እየተፈራረቀባቸው
ስለሆነ በክብር ይነሱ ሲል መጻፉን ተከትሎ የመለስ ፋውንዴሽን መስራች ጉባዔ ሰብሳቢ የሆኑት የቀድሞ ምክትል
ጠ/ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰ ፋውንዴሽኑን አስመልክቶ የካቲት 14 ቀን 2005 ዓ.ም መግለጫ በሰጡበት ወቅት
ተመሳሳይ አቋማቸውን በማንጸባረቅ ሕዝቡ ምስሎቹን እንዲያነሳ ተማጽነው ነበር፡፡
ነገር ግን በተለይ በአዲስአበባ በሁሉም ክፍለከተሞች ይህ ትዕዛዝ ተግባራዊ ሳይሆን 20 ቀናት አልፈዋል፡፡
የአቶ መለስ ምስል እንዲነሳ ቤተሰቦቻቸውን ጭምር በመወከል የተማጽኖ ጥያቄ ያቀረቡት የአቶ አዲሱ ትዕዛዝ
አለመከበሩ የከተማዋ በርካታ ኀብረተሰብ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡
አቶ መለስ በነሃሴ ወር 2004 ዓ.ም በይፋ ሞታቸው ከተነገረ በኋላ በተለይ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ከመጠን ባለፈ ሁኔታ ስብዕናቸውን አግዝፈው በየደቂቃው ሲናገሩና ራዕያቸውም እንደመጽሐፍ ቅዱስ ለመስበክ መሞከራቸው፣ምስሎቻቸውንም በየመንገዱና በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎችና በሕዝብ የትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች ላይ እንዲለጠፍ ማድረጋቸው በህዝቡ ዘንድ ሰውየው ከመሰልቸት አልፈው እንዲጠሉ አድርጎአቸዋል።
በአዲስአበባ የሚገኝ የአንድ ወረዳ አመራር አባል ስለጉዳዩ ተጠይቆ ለአዲስ አበባው ዘጋቢ እንደተናገረው የአቶ መለስ
ምስሎች ከየጎዳናው ላይ እንዲወርዱ አቶ አዲሱ ተናግረዋል መባሉን ከመስማት ውጪ በጽሑፍ የደረሳቸው ነገር
እንደሌለ ጠቅሰው ትዕዛዙ ከልብ ከሆነ በራዲዮና በቴሌቪዥን ሳይሆን በስርዓቱ ትዕዛዙ ሊወርድና ሊደርሰን ይገባ
ነበር ብለዋል፡፡
የአቶ መለስ ፎቶዎች እንዲነሱ ትእዛዝ የሚሰጠው አካል ማነው የሚለው ጥያቄ አሁንም አልተመለሰም። አንዳንድ ወገኖች በቅርቡ የሚካሄደው የኢህአዴግ ጉባኤ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የመለስ ፎቶ ግራፎች ተሰቅለው ሊቆዩ ይችላሉ በማለት ይገምታሉ።