የህወሀት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለድርጅታዊ ጉባኤ መቀሌ ገብተዋል

መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-ካለፉት 21 አመታት ጀምሮ የመንግስትን ስልጣን በበላይነት የያዘው ህወሀት፣ ድርጅቱን ለረጅም ጊዜ የመሩት አቶ መለስ ዜናዊ ካረፉ በሁዋላ ያጋጠመውን የመከፋፈል አደጋ ሸፋፍኖ በማለፍ፣ ከመጋቢት 8 ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት 11ኛ ጉባኤውን የሚያካሄድ ሲሆን፣ በጉባኤው ለመሳተፍ ነባር አመራሩ መቀሌ መግባታቸው ታውቋል። በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑትን አቶ ስዩም መስፍንን ጨምሮ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አ  ድሀኖም እና ሌሎች የፌደራል ከፍተኛ ባለስልጣናት መቀሌ ውስጥ መታየታቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያመለክታል።

በጉባኤው አጀንዳ ላይ መስማማት ተስኖአቸው የቆዩት አመራሮቹ ፣ በመጨረሻ ለጉባኤው የሚሆን አጀንዳ ማዘጋጀታቸው ታውቋል። በከተማው ውስጥ ” ህወሀት እንደ 1993ቱ ልትከፋፈል ነው የሚል ” ወሬ በስፋት እንደሚወራ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ መምህር ለኢሳት ተናግሯል። አብዛኛው ወጣት አዲስ ነገር ይፈጠራል ብሎ ተስፋ እንደማያደርግ  መምህሩ አክሎ ገልጿል።

የህወሀት አርማና የአገሪቱ ሰንደቃላማዎች በብዛት በየ አካባቢው ተሰቅለው መታየታቸው መቀሌን ቢያደምቃትም፣ በፒክ አፕ መኪኖች ላይ ተጭነው ቅኝት የሚያደርጉ እና በየመንገዶች ላይ የፈሰሱ ወታደሮች ከተማዋን በማጨናነቃቸው የጉባኤውን ድባብ ቀንሶታል።

በጉባኤው ማብቂያ እለት ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድጋፉን ለህወሀት እንዲገልጽ ካድሬዎች በመቀስቀስ ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።

አንድአንድ አስተያየት ሰጪዎች ህወሀት ችግር ያልተፈጠረ በማስመሰል ለመሸፋፈን ጥረት ማድረጉን በመተቸት፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ችግሩ ተመልሶ መምጣቱ አይቀርም ይላሉ።