የፍትህ ሚኒስቴር በስራ ላይ ያለውን የይቅርታ አዋጅ የሚያሻሽል አዲስ ረቂቅ ሕግ እያዘጋጀ መሆኑ ተሰማ፡፡

 

መጋቢት ፫(ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሚንስቴሩ  ሕጉን ለማሻሻል የፈለገው እስር ቤቶች በእስረኞች ብዛት እየተጣበቡ በመምጣታቸው ነው ሲሉ ምንጮች ገልጸዋል።
ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በፌዴራልና በክልሎች መንግስታት በሚገኙ እስር ቤቶች ቆይታቸው መልካም ስነምግባርን አሳይተዋል የተባሉ ከ62 ሺ በላይ እሰረኞች ይቅርታ ተደርጎላቸው ከእስር ቤት መውጣታቸው በአዲሱ ረቂቅ ሰነድ ውስጥ ተመልክቷል

እስር ቤቶች በአመክሮ፣በይቅርታ ወይም ሙሉ የፍርድ ጊዜያቸውን ጨርሰው የሚለቀቁ እስረኞች ከእስር ቤት ወጥተው ወደህብረተሰቡ ከተቀላቀሉ በኋላ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር አለመኖሩን እንድክመት ተጠቅሶአል፡፡
የእስረኞችን ሰብዓዊ መብቶች ከማስከበር አንጻር እስር ቤቶች እሰረኞችን አርሞ እና አንጾ የማውጣት አቅማቸው አጥጋቢ አለመሆኑ፣ለእስረኞች የሚቀርቡ የሙያና የቀለም ትምህርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እና በበቂ ሁኔታ  የተዳረሱ አለመሆናቸውን፣የጤና፣የንጹህ መጠጥ ውሃ፣የንጽህና መጠበቂያ ውሃ አቅርቦት መጓደል እንዲሁም የማረሚያ
ቤቶች ጥበትና የመገልገያ ቅሳቁስ አለመሟላት አሁንም የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸው በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።