አሰላ ትናንት በእሳት ዛሬ በመኪና አደጋ ተጠቃች

 

መጋቢት ፫(ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በከተማዋ ትናንት ሌሊት 5 ሰአት ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ከ10 በላይ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ንብረትም ወድሟል። ኮምፒዩተር ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች እና የሙዚቃ መሳሪያዎች መሸጫ ቤቶች በቃጠለው ከወደሙት መካከል ይገኙበታል።

የከተማው ነዋሪዎች ፖሊሶች እና የመስተዳዳሩ ባለስልጣናት ከዝርፊያ ሊታደጉዋቸው እንዳልቻሉ ለኢሳት ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው እለት አንድ ከባድ ተሽከርካሪ መኪና  መስመሩን በመሳት በ4 መኪኖችን ላይ ከወጣ በሁዋላ በመንገድ ላይ የነበሩ ሰዎችን መግደሉን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያመልክቷል።

እስካሁን ባለው መረጃ 6 ሰዎች ወዲያውኑ የሞቱ ሲሆን፣ ክፉኛ ቆስለው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ በርካታ ሰዎችም አሉ።

 

አንድ ወጣት የመኪናው ጎማ ተጭኖት ከሁለት ሰአታት በላይ ከቆየ በሁዋላ ህይወቱ ማለፉን የአይን እማኞች ገልጸዋል። ወጣቱን በህይወት ለመታደግ ያልተቻለው መኪናውን የሚያነሳ የመኪና ማንሻ በመጥፋቱ መሆኑን እነዚህ የአይን እማኞች ገልጸዋል።

የአደጋው መንሰኤ የፍሬን መበጠስ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ገልጸዋል።