የካቲት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በደቡብ ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ የታየው የአማራ ተወላጅ አርሶ አደሮችን የማፈናቀሉ እንቅስቃሴ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ በመተከል ዞን በቡለን ወረዳ በመደገሙ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ አርሶ አደሮች ክልሉን እየለቀቁ እየወጡ ነው። የአይን እማኞች ለኢሳት እንደገለጡት በአሁኑ ሰአት ልጆቻቸውን ይዘው ፣ የቤት እንስሶቻቸውን እየነዱ መንገድ ወደ መራቸው በመጓዝ ላይ የሚገኙት የአማራ ተወላጆች ከ5 ሺ በላይ ናቸው።
ከ500 ያላነሱ አርሶ አደሮች የአማራ ክልል ዋና ከተማ ወደ ሆነቸው ባህርዳር የደረሱ ቢሆንም፣ አቤቱታቸውን የሚቀበላቸው ሰው በማጣታቸው ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸውን ትናንት ባህርዳር የገቡ ተፈናቃዮች ለኢሳት ገልጠዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን ባለስልጣናት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጉርዳፈርዳ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን በተመለከተ ለፓርላማ ሲናገሩ፣ ተፈናቃዮቹ በህገወጥ መንገድ በመሄድ በክልሉ የሰፈሩ ናቸው በማለት መናገራቸው ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም ከደቡብ ክልል የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች የት እንደደረሱ በውል አይታወቅም። የተለያዩ የተቃዋሚ ድርጅቶች የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስት በአማራ ተወላጆች ላይ የሚወስደው እርምጃ ከዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር እንደሚያያዝ ሲገልጹ ቆይተዋል።