የካቲት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት የአዲስ አበባ ወኪል እንደገለጠው ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየው ብርቱካን በአሁኑ ጊዜ በኪሎ እስከ 30 ብር በመሸጥ ላይ ሲሆን፣ አፕል ደግሞ በኪሎ እሰከ 80 ብር እየተሸጠ ነው።
የብርቱካን ዋጋ መጨመር ምክንያቱ በውል ባይታወቅም፣ ብርቱካን በሚያመርቱ ቆላማ አካባቢዎች የሚታየው የዝናብ እጥረት ዋነኛው ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።
በገበያ ላይ የሚቀርቡት ብርቱካኖች የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ ቢሆንም፣ እንደልብ ለማግኘትም አስቸጋሪ ሆኗል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባን በመሳሰሉ ከተሞች የሚሸጠው አፕል ፣ ደሀው ህዝብ በአይኑ አይቶት የሚያልፍ እንጅ የሚቀምሰው አልሆነም። በቀን 20 ብር የሚያገኝ ሰራተኛ አንድ ኪሎ ብርቱካን ለመግዛት የማይችልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ፣ ምናልባትም ብርቱካንም በቅርቡ የሀብታሞች ምግብ ተብሎ ሊመደብ እንደሚችል ዘጋቢያችን ገልጧል።