የ ጆሀንስበርግ ቅድስት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን በውጭ የሚገኘውን ቅዱስ ሲኖዶስ እንደምትደግፍ አስታወቀች

የካቲት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-በደቡብ አፍሪካ በጆሀንስበርግ ከተማ የምትገኘው ጽርሐ አርያም ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን  ለኢሳት በላከችው መግለጫ ”   መንግሥት ራሱ ያወጣውን ሕገ-መንግሥትና ዓለም አቀፉን ሕገ ቤተክርስቲያን በመጣስ በቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን ላይ ግልጽ ተጽእኖና ጫና በማድረግ፤ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲካሔድ የቆየው የዕርቀ ሰላም ጥረት ከፍጻሜ እንዲደርስ በማይፈልጉ ጵጵስናን የተከናነቡ ጥቂት ካድሬዎቹ አማካይነት ቅዱስ ሲኖዶስ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ የተጀመረውን የሰላምና አንድነት ውይይት ለውጤት እንዳያበቃ በማወክ ኦርቶዶክሳውያን ባልጠበቁት አሳዛኝ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ” አድርጓል ብላለች።

ቤተክርስቲያኑዋ ” የዕርቀ ሰላሙን ውጤት በጸሎትና በታላቅ ተስፋ ሲጠባበቅ የቆየውን እና መንግሥት በኀይሉና በጉልበቱ በመመካት ለሁለተኛ ጊዜ ሕገ-ወጥ ፓትርያርክ በመሾም በፈጸመበት በደል ታላቅ መርዶ የወደቀበትን መላውን ሕዝበ ክርስቲያን ለማጽናናት በስደት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያደርገውን ማንኛውንም መንፈሳዊ እንቅሥቃሴ ከጎኑ በመሆን ” እንደምትደግፍ ግልጽ አድርጋለች።

ላለፉት 21 አመታት ተከፋፍላ የቆየችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አቡነ ጳውሎስ ካረፉ በሁዋላ ወደ አንድነት ለመምጣት ሰፊ እድል የነበራት ቢሆንም፣ በመንግስት ጣልቃ ገብነት የተነሳ እድሉን ሳትጠቀምበት መቅረቷን ብዙዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።