ኢሳት ዜና:- እስካሁን ወደ 65 የሚጠጉ ሰዎች መታሰራቸው የታወቀ ሲሆን፤ የአካባቢው ህዝብም በመንግስት ላይ ማኩረፉ እየተነገረ ነው።
የኢሳት ወኪሎች እንዳጠናቀሩት መረጃ ከሆነ፤ውጥረቱ ይበልጥ እየተባባሰ የመጣው፤ ከሁለት ሳምንት በፊት በወረዳቸው፣ በዞናቸውና በቀበሌያችው በተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት፣
ለችግር መጋለጣቸውን አዲስ አበባ በመምጣት ለመገናኛ ብዙሀን ይፋ ያደረጉ የአርሶ አደሮች ተወካዮች ለእስር መዳረጋቸውን ተከትሎ ነው።
በመጀመሪያ የታሰሩት፤ አቤቱታ ለማቅረብ አዲስ አበባ የመጡት አቶ ዳሞታ ኡቃ፣ አቶ ዶኮ ኮዶ ፣ አቶ ዳንኤል ዳርዬ እና ሌሎች የቀበሌው ሶስት አርሶ አደሮች ሲሆኑ፤ አሁን ግን የታሳሪዎቹ ቁጥር አስከ 65 እንደሚደርስ ተነግሯል።
“አዲስ አበባ ድረስ ሄዳችሁ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳዩን ተናግራችኋል” በሚል ሰበብ የአካባቢው ፖሊስ አርሶ አደሮቹን ማሰሩን የጠቀሱት ምንጮች፤ እስረኞቹም፤- በላንቴ ፣ በጨንቻ እና በአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ምንጮች እንደሚሉት፤ “አለ” በተባለው ችግር ዙሪያ ማጣራት እንዲያካሂዱ ከተመረጡ የአጣሪ ቡድኑ አባላት መካከልም፤ ሁለት የቀበሌው የግብርና ባለሙያዎች ከስራ ታግደዋል። አንዳንድ የላንቴ ቀበሌ ወጣቶችም እስርን በመፍራት ወደ አርባ ምንጭ ከተማ እየሸሹ እንደሆነ ተናግረዋል።
“ ባለፈው ሳምንት፦ “ስብሰባ ስላለ፤ ፖሊስ ጣቢያ ድረስ መጥታችሁ ተሰብሰቡ” የሚል ትዕዛዝ በየቀበሌው መስተዳድሮች አማካይነት ሲተላለፍ፤ ህብረተሰቡ “መሰብሰቢያ አዳራሽ እያለ ፖሊስ ጣቢያ ግቢ ውስጥ አንሰበሰብም”ማለቱን ተከትሎ በርካታ ሰዎች መታሰር እንደጀመሩ መዘገባችን አይዘነጋም።
በስፍራው የሚንቀሳቀሱት የኢሳት ወኪሎች የላኩት ዜና እንደሚያመለክተው፤ የመንግስት ታጣቂዎች በህብረተሰቡ ተወካዮች ላይ የወሰዱት የጅምላ እሰር እርምጃ፤ በአሁኑ ጊዜ ውጥረቱንና ፍጥጫውን እጅግ አባብሶታል።
እንደ ወኪሎቻችን ሪፖርት፡በተወሰደው እርምጃ ያኮረፈው የአካባቢው ህዝብ፤“መልካም አስተዳደር አጥተናል”ለሚለው አቤቱታችን የመንግስት ምላሽ እስር ከሆነ፤ ከእንግዲህ የምናደርገውን እናውቃለን “ እያለ ይገኛል።