አቶ መለስ “በህዳሴው ዋዜማ ላይ እንገኛለን” እያሉ በሚናገሩበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዳቦ እጥረት እየታመሰች መሆኗ ተዘገበ።

ኢሳት ዜና:- ከ ዛሬ 20 ዓመት በፊት ስልጣን ላይ ሲወጡ የላቀው ምኞታቸው በ 10 ፤ ቢበዛ በ 15 ዓመት ውስጥ የ ኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሶስት ጊዜ ሲበላ ማዬት እንደሆነ አቶ መለስ ዜናዊ መናገራቸው ይታወሳል ።

ይሁንና ከ20 ዓመት የስልጣን ቆይታቸው በኋላ በኢትዮጵያ መሬት ላይ በተጨባጭ የታየው ነገር አስከፊ ድህነትና ረሀብ መሆኑን፤ የአገዛዙ ገፈት ቀማሽ የሆኑት እጅግ ብዙሀኑ ኢትዮጵያውያን ይናገራሉ። ዘይትና ሳሙና እንደ ቅንጦት ዕቃ ከክዋክብት በላይ የራቁት የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ደግሞ በዳቦ እጥረት እየታመሰ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ የሚወጡት ዜናዎች ያመለክታሉ።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ችግሩ የተከሰተው በስንዴ ዱቄት አለመኖር ነው ሲል አስታውቋል- ምንም የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት በመጋዘን ውስጥ በቂ ክምችት አለ በማለት ለማስተባበል ቢሞክርም። የስንዴ ዋጋ በተለዬ መልኩ ካለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ እጅግ እየናረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።ይህም በመሆኑ በመጋዘን የነበረው ክምችት ላለፉት አምስት ወራት በንግድ ሚኒስቴር አማካይነት ለየ ዳቦ ቤቶች በረሽን መልክ ሲከፋፈል ቆይቷል። ይሁንና የነበረው ክምችት እየተሟጠጠ በመምጣቱ ከመስከረም ወር ጀምሮ ዳቦ ቤቶች በከፍተኛ ደረጃ የዱቄት እጥረት አጋጥሟቸዋል።

የዱቄት እጥረቱን ተከትሎ በርካታ ዳቦ ቤቶች  የዳቦ ግራምን ለመቀነስ ተገደዱ። የዳቦዎች መጠን ያለቅጥ ማነስ እያነጋገረ ባለበት ሰዓት  ይባስ ብሎ በመዲናይቱ ከሚገኙ ዱቄት ፋብሪካዎችና ዳቦ ቤቶች መካከል  አብዛኞቹ ስራቸውን ማቆማቸው ተሰማ። የሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀሀዬ ዘሙ፤ በዱቄት እጥረት ምክንያት በአዲስ አበባ ውስጥ ካሏቸው 65 ዳቦ ቤቶች 45 ቱን መዝጋታቸውን አስታውቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ  በቀን እስከ 350 ቶን ዳቦ የመጋገር አቅም ያለውን የዳቦ ማምረቻ ኢንደስትሪያቸውን መዝጋታቸውን አቶ ፀሀዬ ተናግረዋል። ያለቻቸውን ቀሪ ዱቄት እንደምንም በመጠቀም  እየሰሩ የሚገኙ የተወሰኑ ዳቦ ቤቶችም፤ እየጋገሩት ያለው የዳቦ መጠን እያነሰ መምጣቱን ነዋሪዎች ይናገራሉ::

የዳቦ እጥረቱ የተፈጠረውም ሆነ የተባባሰው በስንዴ ስርጭት  ላይ በተከሰተ የአፈፃፀም ችግር ነው የሚለው የንግድ ሚኒስቴር ፤አዲስ የስንዴ ስርጭት መመሪያ ማውጣቱን ገልጿል። መንግስት በበኩሉ  ለተከሰተው ችግር እንደተለመደው በድፍኑ ባለዱቄት ፋብሪካዎችንና ባለ ዳቦ ቤቶችን፡” ተጠያቂ ለማድረግ ሞክሯል። “ችግሩ ሊፈጠርና ሊባባስ የቻለው፤ዱቄት ፋብሪካዎችና ዳቦ ቤቶች ሀላፊነታቸውን ባግባቡ ባለመወጣታቸው ነው “በማለት።

መንግስትም  ይህን ቢልም ፤ የንግድ ሚኒስቴርም  ችግሩን ለመሸፋፈን ቢሞክርም፤ የአዲስ አበባ የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ ግን ችግሩ የተፈጠረው በስንዴ ዱቄት ጠቅላላ አለመኖር ነው በማለት ነው ሀቁን የተናገሩት::

የእህል ንግድ ድርጅት የስራ ሃላፊ  በአሁኑ ጊዜ ከ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ዱቄት ከውጪ አገር ተገዝቶ ወደ አገር ቤት እየገባ ነው ይላሉ። ከዚህም ውስጥ 900 ሺህ ኩንታሉ በእህል ንግድ ድርጅት መጋዘን ደርሶ ለስርጭት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ ማረሚያ ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች በመደበኛ ፕሮግራም ዘወትር ዳቦ ማግኘት ያለባቸው  ተቋማት  በችግሩ እንዳይመቱ መንግስት ስጋት ላይ መሆኑም ታውቋል። በንግድ  ሚኒስቴር የ ኢንስፔክሽንና ሪጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ወልደሥላሴ እንዳሉት በተለይ በተጠቀሱት ተቋማት እጥረቱ እንዳይከሰት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። “ችግሩ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉት ክልሎችም አሣሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን፤ የ ኢሳት ዘጋቢዎች ያጠናቀሩት ሪፖርት ያመለክታል።

ባለፉት 20 ዓመታት የ ኢህአዴግ የልማት መርሀ ግብር ዋነኛ ማዕከል ነው የተባለው የገጠሩ ኢትዮጵያ ክፍል በረሀብ እየተቀጣ በሚገኝበትና  የከተማው ነዋሪም ዘይትና ሳሙና እስከሚያጣ ድረስ በአስከፊ ድህነት በወደቀበት  ጊዜ፤ አቶ መለስ ዜናዊ “እንደገና”በሚል ርዕስ ከወራት በፊት በ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባሰሩት ፊልም፤-“ በህዳሴ ወይም በትንሳኤ ዋዜማ ላይ እንገኛለን” ማለታቸው ይታወሳል።

አቶ መለስ ከዚህም አልፈው፦የኢትዮጵያን ዕድገት- ጃፓኖች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ካሳዩት ትንሳኤ  ጋር በማመሣሰልና፤ ጃፓኖች ዕድገት ማስመዝገብና መነሳት ሲጀምሩ እንጢጥ እንጢጥ ማለት በማብዛታቸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ዋጋ መክፈላቸውን በማስታወስ፦ ”እኛ ግን እየተነሳን ቢሆንም፤ እንደነሱ  እንጢጥ እንጢጥ ማለት የለብንም” እስከማለት ደርሰዋል።

አቶ መለስ ይህን ያሉት፤ ከሁለት ሰዓታት በፊት ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሀን ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው ድርቅና ረሀብ አጥንታቸው የገጠጡ ሰዎችንና በየቦታው የወዳደቁ የእንስሳት በድኖችን  ካሳዩ በሁዋላ መሆኑ፤ በወቅቱ ብዙዎችን ”አቶ መለስ የሚያወሩት ስለየትኛዋ ኢትዮጵያ ነው” ማሰኘቱ ይታወቃል።

እነሆ አቶ መለስ በትንሳኤው ዋዜማ ነን ባሉ በጥቂት ወራት  ውስጥ ፦”የዳቦ ቅርጫት” ተብላ ትጠራ የነበረችው አገር – በዳቦ እጥረት እየታመሰች ትገኛለች። “የሚበላውን ያጣ ህዝብ፤ መሪዎቹን ይበላል”በማለት ዶክተር መረራ ጉዲና በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ መቆየታቸው  አይዘነጋም።