ኢሳት የአጭር ሞገድ ሬዲዮ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ መጀመሩን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ፣

መስከረም 26 2004 ዓ.ም
የኢሳት ማኔጅመንት እና መላው የኢሳት ቤተሰቦች የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ እና ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት አለው በሚል እምነት ከተነሳን አንድ ዓመት ተሻገርን፤ ይህንንም  ከግብ ለማድረስ ማናቸውንም መሰናክል ሰብረን ለማለፍ ባልተቋረጠ ትግል ውስጥ ቀጥለናል። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳሳወቅነው የኢትዮጵያ ህዝብ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ማግኘት ተፈጥሮዓዊና  ሰብዓዊ መብቱ ነው። ስልጣን ላይ ያለው የአቶ መለስ መንግስት ይህንን መብት ገፎ የፈለገውንና የሚስማማውን ዜና እና መረጃ ካልሆነ በቀር ሌላ ነጻ እና ሚዛናዊ መረጃ ለህዝብ እንዳይደርስ በሚቻለው ሁሉ ሌት ተቀን ጥረት እያደረገ ይገኛል፤ በዚህም ከውጭ የሚሰራጩ የቴሌቪዥን፣ የራዲዮና የኢንተርኔት ስርጭቶችን ማፈን እና ማወክ መንግስታዊ ተግባሩ ሆኖ ቀጥሏል። ይህንን ተግባሩን የተሳካ ለማድረግ የውጭ ምንዛሪ የሚከፈላቸው የባዕድ ቅጥረኞች እስከ ማሰማራት ደርሷል፤ በዚህ በውጭ ባለሙያዎች ድጋፍ በሚደረገው  የአየር ሞገድ ጥቃት ዋነኛ ኢላማ ሆኖ የወጣው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ነው።

ኢሳት በተደጋጋሚ ለአፈና ጥቃት በተጋለጠበት ጊዜ ለህዝብ በግልጽ ቃል የገባው አንድ መሰረታዊ ጉዳይ አለ፣ ዛሬም እንደገና ይህንኑ ቃሉን ያድሳል። ይኸውም ኢሳት ሚዛናዊ፣ እውነተኛና ተዓማኒ የመረጃ ምንጭ በመሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነት፣ ለእኩልነትና ለዴሞክራሲ ለሚያደርገው ትግል የራሱን አስተዋጽዖ ማድረግ ነው። ይህንንም ቃሉን ተግባራዊ ለማድረግ ማንኛውንም ዓይነት አፈና በመቋቋም ወደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ለመድረስ የተለያዩ አማራጮችን እንደሚከተል ባሳወቀው መሰረት እነሆ ዕለታዊ  የአጭር ሞገድ ሬዲዮ ጀምሯል። በኢትዮጵያ እና  በአካባቢው ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውን ዘውትር ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት በአጭር ሞገድ (SHORT WAVE) በ15370 khz  19 MB  የኢሳትን ሬዲዮ ማድመጥ ይችላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የኢሳት ቴሌቪዥንን የ24 ሰዓት ስርጭት ለዘጠነኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለማስተላለፍ ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፤ ድረ ገጹን በአዲስ መልክ እያደራጀን እንገኛለን፤ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትያጵያውያን በኢንተርኔት የሚያገኙትን የኢሳት ፕሮግራሞች በቴሌቪዥን ስክሪን ለማየት የሚያስችል IPTV በሚባል ቴክኖሎጂ ለማቅረብ እየተዘጋጀን ነው። የኢሳትን ፕሮራሞች ከቤትም ውጭ በተንቀሳቃሽ ስልኮች ስማርት ፎን (SmartPhone) ለመከታተል እንዲችሉ ዝግጅቱ እያጠናቀቅን ነው። የነጻነት ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ልሳን የሆነው ኢሳት እነዚህን ሰፊ ፕሮጀክቶች በዘላቂነት ለማስኬድ ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልገዋል፤ ስለሆነም በሀገራችን ኢትዮጵያ ነጻነት እንዲመጣ፣ እኩልነት እንዲሰፍን፣ ዲሞክራሲ እንዲያብብ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን  ሁሉ  ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ጥሪ እናቀርባለን። እሰከዛሬም ድጋፋቸው ላልተለየን ምስጋናችንን እናቀርባለን።

ኢትዮጵያ ለሚገኙት ቤተሰቦ ይህንን ዜና እንድታስተላልፉልን በትህትና እንጠይቃለን።
ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ ዓይን እና ጆሮ ነው!!!

የኢትዮጵያ ህዝብ እውነተኛ መረጃ የማግኘት ሰብዓዊ መብት አለው!!!

የኢሳት አስተዳዳር

www.ethsat.com