የኢሳትን ወደ ፕሮግራም ሥርጭት መመልስ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ፣

ሰኔ 3፣ 2003 ዓም

ከሁለት ወር በላይ በደረሰበት ከፍተኛ የዓየር ሞገድ የፕሮግራሙን ሥርጭቅ አቁሞ የነበረው ኢሳት በሰኔ 2፣ 2003 ዓም ወደ መደበኛ
ሥርጭቱ መመለሱን ለህዝብ ይፋ ሲያደርግ በታላቅ ደስታ ነው። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ማንም ሊከለክልህና ሊገድብብህ
ሥልጣን የሌለውን እውነተኛ መረጃ የማግኘት ተፈጥሯዊ መብትህን ለማፈን እና እነርሱ የፈለገውን የውሸት ትርኪ ምርኪ ካልሆነ
በቀር፣ ሌላ ምንም ዓይነት መረጃ እንዳታገኝ፣ በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ቀን ከለሊት በደሀ ህዝብ ሥም ለምኖ ባመጣው ከፍተኛ
የውጭ ምንዛሪ በሚከፈላቸው የቻይና ቅጥረኞችን በማሰማራት ኢሳትን በተደጋጋሚ ለማፈን ተንቀሳቅሷል። ይህም በመሆኑ በተለያዩ
ጊዚያት ሥርጭታችንን ለማቋረጥ ተገደናል።
ይህ ሁኔታ በተለይ በሀገር ውስጥ ያለውን ወገናችንን ምን ያህል እንደሚያሳስዝነው በተለያዩ መንገዶች የሚደርሱን መልዕክቶች
በግልጽ ያስረዳሉ። በኢሳት አካባቢ ያለን ወገኖች አንዳንዶቹን መልዕክቶች እንባ እየተናነቀን ነው የምንሰማቸው። የነጻነት የሲቃ
ድረሱልን ጥሪዎች፣ እባካችሁን ቀን አታጨልብን የሚሉ ልብ የሚሰብሩ መማጸኖች፣ የሰማ ህሊናችን የሚያስፈልገውን መስዕዎትነት
ከፍለን እየወረድንም እየወጣንም በምንም የማንተወው ጉዳያችን እንዲሆን አድርጎታል።
ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ይህ አስከፊ አፈና በምንም ማሸነፍ የለበትም በሚል ከፍተኛ ስሜት እርዳታ ለሚያደርጉልን በአብዛኛው
በውጭ ሀገራት የምትገኙ ወገኖች፣ የፈለገው አፈና ቢካሄድብንም፣ የፈለገው ሴራ ቢሴርብንም፣ የፈቀደው ደንቃራ ቢደረግብንም፣
እውነተኛ እና ሚዛናዊ መረጃ ለወገናችን እየወደቅንም እየተነሳንም ለማቅረብ ዛሬም እንደገና በድጋሚ ቃል እንገባለን።
እንዲያውም በቅርብ ጊዜ በKU ባንድ ተጭማሪ ማስተላለፊያ ጣቢያ ለመክፈት ያለንን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የመጨረሻውን
ዝግጅት እያጠናቀቅን መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ልንገልጽላችሁ እንወዳለን። ከዚህ በተጨማሪ ለወደፊቱ በበርካታ ጣቢያዎች ኢሳትን
በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ለማስተላለፍ የምንችልበትን ዕቅድ አውጥተን መጨረሳችንን ስንገልጽ በታላቅ ደስታ ነው።
አዲሱ የስርጭት መረጃ፣
ABS1 Satellite
75 degree East
C Band
Down link : 3.480 GHz Vertical (3480)
Symbol Rate: 1.852 Msps (1852)
FEC : 2/3
ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ ዓይን እና ጃሮ ነው!!!
የኢትዮጵያ ህዝብ እውነተኛ መረጃ የማግኘት ተፈጥሯዊ መብት አለው!!!
ኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን፣
ሰኔ 2003 ዓ.ም
www.ethsat.com