ታህሳስ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ተገድለው ያልተነሱ ውሻዎች በህብረተሰቡ ዘንድ የጤና ስጋት መፍጠራቸውን ፋና ዘገበ።
ራዲዮ ጣቢያው የመዲናዋን ነዋሪዎች በመጥቀስ እንደዘገበው ሰሞኑን ባልተለመደ መልኩ በተለያዩ የመዲናይቱ አካባቢዎች የሞቱ ውሾች ይታያሉ።
የህብረተሰቡን ጥቆማ መሰረት በማድረግ የራዲዮ ጣቢያው ጋዜጠኞች በከተማዋ ባደረጉት ቅኝት በስታድየም ፣ በጨርቆስ ፣ በፒያሳና በገርጂ መብራት ሃይል አከባቢዎች የተገደሉ ውሻዎች ባልተለመደ መልኩ ቁጥራቸው በርክቶ መመልከታቸው ተገልጿል ።
ባለቤት አልባ ውሻዎችን በዘመቻ መልክ የማስወገድ ሃላፊነት የተሰጠውና ስራውን የሚያከናውነው የከተማዋ አስተዳደር የከተማ ግብርና የስራ ሂደት ፤ክስተቱን ሰሞኑን ካካሄደው ውሻዎችን የመግደል ዘመቻ ጋር አያይዞታል ።
የስራ ሂደቱ ሰሞኑን ባለቤት አልባ ውሻዎችን የማስወገድ ስራ ያከናወነ ሲሆን ፥ አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ የተፈጠረው ወሻዎች መርዙን ከበሉ በኋላ ወድያው ባለመሞታቸውና ራቅ ወዳለ ስፍራ ሄደው በመሞታቸው ነው ብሏል።
<<ሟች ውሻዎቹን የማንሳት ሃላፊነት ያለበት የአዲሰ አበባ ከተማ ፅዳት ኤጀንሲ ነው >> ሲልም የሞቱትን ውሾች የማንሳቱ ሥራ እሱን እንደማይመለከተው አስታውቋል።
የከተማዋ ጽዳት ኤጀንሲ ግን በዘመቻ የሚገደሉ ባለቤት አልባ ውሻዎችን የማንሳቱን ስራ ከአስተዳደሩ የከተማ ግብርና የስራ ሂደት ጋር በጋራ እንደሚሰራ በመግለጽ፤ <<የማንሳቱ ሥራ የ ኤጅንሲው ብቻ ነው>> የሚለውን እንደማይቀበለው ነው ያመለከተው።
ኤጀንሲው አክሎም እንደውም ሰሞኑን ስለተካሄደው ዘመቻ መረጃ የለኝም ብሏል ።
የአስተዳደሩ የከተማ ግብርና ሂደት እና የመዲናይቱ የጽዳት ኤጄንሲ ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማሸሽ እርስበርስ ጣታቸውን ከመቀሳሰር ውጪ የህብረተሰቡ ስጋት በምን መልክ እንደሚፈታ ያሉት ነገር የለም።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አከባቢዎች አንሺ ያጡት የሞቱ ባለቤት አልባ ውሻዎች ሁኔታ ለነዋሪው ጤና ጠንቅ እንዳይሆኑ ሁለቱ ወገኖች ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚገባቸው ማሣሰቢያ ተሰጥቷል።